ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በጀግንነት በመጠበቅ ለሀገር አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ሁልጊዜም ዝግጁ ነን

አሶሳ፤ ጥቅምት 14/2019 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በጀግንነት በመጠበቅ ለሀገር አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ሁልጊዜም ዝግጁ ነን ሲሉ በሀገር መከላከያ የምዕራብ ዕዝ የሠራዊት አባላት ተናገሩ።

የዘንድሮው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን በነገው ዕለት "የድል ሥራዊት" በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት ይከበራል።

ቀኑን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው በሀገር መከላከያ ሠራዊት የምዕራብ ዕዝ 404ኛ ሕዳሴ ኮር የሠራዊት አባላት እንደገለጹት፣ ሠራዊቱ በየተሰማራበት ግዳጅ የተሰጠውን ተልዕኮ በፅናትና በጀግንነት በመወጣት የሀገርን ሰላም እና የህዝብን ደህንነት እያስጠበቀ ይገኛል።

የዕዙ 404ኛ ሕዳሴ ኮር አባል አስር አለቃ ፈርሃን እስማኤል፤የመከላከያ ሠራዊት ቀን ሲከበር ሀገርን ለማፅናትና ሰላምን ለማስጠበቅ ትናንት የተከፈለውን መስዋዕትነት በማስታወስና ለዛሬው ተልዕኮም ዝግጁነታችንን በማረጋገጥ ሊሆን ይገባል ብሏል።

የቀኑ መከበር ሠራዊቱ ከህብረተሰቡ ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ይበለጥ ያጠናክራል ያሉት አስር አለቃ ፈርሀን፣ በዓሉ ሀገርን ለማጽናት የተከፈለውን መስዋዕትነት ለማሰብና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መረጋገጥ ያለንን ሃላፊነት ዳግም የምናረጋግጥበት ነው ሲል ገልጿል፡፡

ሠራዊቱ በአሁኑ ወቅት ከውጭና ከአገር ውስጥ ሊቃጣ የሚችልን ማንኛውንም ጥቃት በአስተማማኝ መንገድ መክቶ ማክሸፍ የሚያስችል አቅምና ዝግጅት እንዳለውም ተናግሯል።

የምዕራብ ዕዝ 404ኛ ሕዳሴ ኮር አባል መቶ አለቃ ባባው ዘውዴ እና ምክትል መቶ አለቃ መለሰች ተሰማ በበኩላቸው፤ መከላከያ ሠራዊት በተሰማራባቸው ግንባሮች ሁሉ ግዳጁን በአሸናፊነት የመወጣት አቅሙን እያሳደገ ነው ብለዋል። 

በሠራዊቱ ውስጥ የድል አድራጊነት ባህል እያደገ መምጣቱን የተናገሩት አባላቱ፣ ዛሬም ሠራዊቱ ተልዕኮውን በብቃትና በጀግንነት በመወጣት የሀገርን ሉዓላዊነት እያስከበረ ይገኛል ብለዋል።

ሠራዊቱ የድል ሠራዊት መሆኑን ጠቅሰው፣ ህዝብን ደጀን በማድረግ የሀገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅና ሰላምን በዘላቂነት ለማስቀጠል ምንጊዜም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከሀገር ውስጥ ባለፈ በውጭ ሀገራት ጭምር ሰላምን በማስከበር ኢትዮጵያ ያላትን ክብር ከፍ ያደረገ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የሠራዊቱ አባል ኮሎኔል አስታጥቄ አሻግሬ ናቸው።

የ404ኛ ሕዳሴ ኮር ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ደህንነት ጨምሮ በአካባቢው የተሰጠውን  ተልዕኮ በብቃት እየተወጣ መሆኑን ተናግረው፣ ሠራዊቱ ዛሬም የድል አድራጊነት ተልዕኮውን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል ብለዋል።

ኮሩ ከክልሉ የፀጥታ አካላት እና ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በቀጠናው አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም