ቀጥታ፡

የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ክብርና ሉአላዊነት ያስከበረ ጀግና ሰራዊት ነው

አርባ ምንጭ ፤ ጥቅምት 14/2019 (ኢዜአ):- የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ክብርና ሉአላዊነት ያስከበረ ጀግና ሰራዊት መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቀን "የድል ሰራዊት" በሚል መሪ ሃሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በነገው ዕለት በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ የኢዜአ ሪፖርተር በአርባ ምንጭ ከተማ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ክብርና ሉአላዊነት ያስከበረ የሚያኮራ ጀግና ሰራዊት መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ለዚህ ጀግና ሰራዊት ተገቢውን ክብርና እውቅና መስጠት እንደሚገባ አንስተዋል።

ከጥንት እስካሁንም በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ የኖረችው ሀገር ዛሬም በቁርጥ ልጆቿ ክብሯና ሉአላዊነቷ እንደተጠበቀ መቀጠሉን ገልጸዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የቀድሞ መከላከያ ሠራዊት አባል አበበ ብምአሎ፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ከአባቶቹ የተረከበውን ጀግንነት አስቀጥሎ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዞ የሀገሩ አስተማማኝ ዘብ መሆኑን በተግባር እያሳየ ይገኛል ብለዋል።

በመሆኑም የሀገር ኩራት የሆነው መከላከያ ሠራዊት የላቀ ክብርና ምስጋና የሚገባው የሀገር ባለውለታ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ተዘራ ቃጻዮ፤ መከላከያ ሰራዊት በጀግንነት ለሀገር እየከፈለ ያለውን ዋጋ ትውልዱ በቅጡ ሊያውቀውና ሊረዳው ይገባል ብለዋል።

 

ለዚህም የሰራዊቱ ቀን በየአመቱ መከበሩ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተው ሁላችንም ለሰራዊታችን ተገቢውን ክብር  መስጠት አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በተገነባው ዘመናዊ ሰራዊት ክብርና ኩራት ተሰምቶናል ብለዋል።

በአንድ ሀገር ጠንካራ ሰራዊት መገንባት ከሉአላዊነትም ያለፈ ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተው ለሰራዊቱ አብሮነትና ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም