ቀጥታ፡

የመደመር መንግሥት የቱሪዝም ልማት ኢትዮጵያን የመስህብ ማዕከል እያደረጋት ነው

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 14/2019 (ኢዜአ):-የመደመር መንግሥት የቱሪዝም ልማት ኢትዮጵያን የመስህብ ማዕከል በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እያሳደገ መሆኑን የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ

የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የብዝኅ ኢኮኖሚ ልማት የለውጥ አብዮትን በማፋፋም ተከታታይ ዕድገት እንዲመዘገብ እያስቻለ ይገኛል።

የመደመር መንግሥት የግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና አይሲቲ የኢኮኖሚ ልማት አምዶችም የሀገራችን የማንሰራራት ዘመን በማብሰር ተወዳዳሪና ዘላቂ የኢኮኖሚ አቅም እየገነቡ ነው።

የቱሪዝም ዘርፍ ከአምስቱ የኢኮኖሚ አምዶች መደረጉም ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ፣ ኃይማኖታዊና ባህላዊ የመስህብ መዳረሻ ሥፍራዎችን የልማት አቅሞች ወደ ዕድል መቀየር አስችሏል።

በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ ተግባራዊ የተደረጉ የልማት ተነሳሽነቶች የሀገራችንን ልክና መልክ መግለጥ ችለዋል።

ይህም የኢትዮጵያን ጸጋዎች ከዘመናዊ የመስህብ መዳረሻ ጋር በማሰናሰል የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ የሚያራዝም ምቹ የማረፊያ ምኅዳር በመፍጠር የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እያሳደገ ነው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የዘርፉ ባለድርሻ አካላት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ልማት ዘመናዊ የመዳረሻ መሰረተ ልማት እንዲፈጠር በማስቻል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እያሻሻለ ነው።


 

የሰለብሪቲ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት አሸናፊ ካሳ፤ ኢትዮጵያ ማራኪ የመስህብ ሥፍራ ያላት ቢሆንም የመዳረሻ እጥረት ለጎብኝዎች ፈታኝ እንደነበር አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም የቱሪዝም ዘርፉን ለማሻሻል የተወሰደው ውጤታማ የልማት እርምጃ የመዳረሻ አማራጮችን በማስፋት የቱሪስቶችን ፍሰትና ቆይታ በማራዘም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የሬፍትቫሊ ኤክስፔዴሽንስ አስጎብኚ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሐሪ መሰለ በበኩላቸው፤ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት የኢኮኖሚ አቅም እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የገበታ ለሸገር፣ ለሀገርና ለትውልድ ፕሮጀክቶችም ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የመስህብ መሰረተ ልማትን በመፍጠር የጎብኝዎችን ፍስትና የቆይታ ጊዜ ማራዘም ያስቻለ ዕድል እየፈጠረ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቱሪዝምና ሆቴል ማኅበር ፕሬዝዳንት ጌታሁን አለሙ ፤ ለቱሪዝም ልማት የተሰጠው ትኩረት የሆቴልና የአገልግሎት ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የመደመር መንግሥት ቱሪዝምን የብዝኅ ኢኮኖሚ አካል ማድረጉም የዘርፉን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያሳደግ ውጤታማ የፖሊሲ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ የሆቴል ባለቤቶች ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት ብሌን ኃይሉ በበኩላቸው፤ የቱሪዝም መዳረሻ መሰረተ ልማቶች የሆቴልና አገልግሎት ዘርፉን የተሰናሰለ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው ብለዋል።


 

የመደመር መንግሥት የቱሪዝም ልማትም ኢትዮጵያን የመስህብ ማዕከል በማድረግ ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሁንዴ ከበደ ፤ የመደመር መንግሥት የቱሪዝም ዘርፍ ጸጋን በመለየት የፈጠረው አስቻይ ምኅዳር የዕይታ ለውጥ ውጤት ነው ብለዋል።


 

ይህም የረጅም ዘመን ያለውን የቱሪዝም ሃብት ወደ ዕድል በመቀየር አዲስ አበባን የሀገራዊ፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የኮንፈረንስ ቱሪዝም የስበት ማዕከል እያደረጋት መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ሁለንተናዊ የልማት እመርታም የቱሪዝም ኢንዱስትሪን አቅም የሚያጎለብት የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ጎብኝዎችን ፍሰት ማሳደግ እያስቻለ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም