የመደመር መንግስት የማይጠናቀቅ ፕሮጀክት አይጀምርም! - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግስት የማይጠናቀቅ ፕሮጀክት አይጀምርም!
ጥቅምት 14/2019 (ኢዜአ):- የመደመር መንግስት የማይጠናቀቅ ፕሮጀክት አይጀምርም!
የአንድ ሀገር የልማት ጉዞ የሚለካው በታቀዱ ፕሮጀክቶች ሳይሆን፤ በተያዘላቸው ጊዜ ተገንብንተው ተጠናቀው ለሀገር በሚኖራቸው ፋይዳ እና በሕዝብ ሕይወት ላይ በሚያመጡት ተጨባጭ ውጤት ነው። የልማት ፕሮጀክቶች የሀገርን ኢኮኖሚ ከማሳደግ ባለፈ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ የማሻሻል፣ የሥራ ዕድሎችን የመፍጠር፣ የምርታማነት አቅምን የማሳደግና ለቀጣይ ትውልድ የተሻለች ሀገር የማስረከብ አላማ የሰነቁ ናቸው። በመሆኑም የመደመር መንግስት እነዚህን መሰረታዊ መርሆዎች በማንገብ ለሀገር ልማት፣ እድገትና ማንሰራራት በትጋትና በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል። የመደመር መንግስት የማይጠናቀቅ ፕሮጀክት አይጀምርም፤ የዚህ መርህ ውጤት ማሳያዎችም ባለፉት ስምንት ዓመታት የተከናወኑና የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ማሳያ ናቸው።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተለያዩ የፋይናንስ፣ የቴክኒክና የዲፕሎማሲ ፈተናዎች ውስጥ አልፎ በመደመር መንግስት ጽናትና በህዝቡ ድጋፍ ተጠናቆ ለአገልግሎት በቅቷል። የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት ባለፈ ለኢንዱስትሪ ዕድገት፣ ለኢኮኖሚ መስፋፋት፣ ለቀጣናዊ የልማት ትስስርና የጋራ ተጠቃሚነት ትርጉሙ የላቀ መሆኑ ይታወቃል። ኢትዮጵያዊያን ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ የማጠናቀቅ አቅምና ችሎታ ስለመኖሩ ተግባራዊ ምላሽ የሰጠና የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ድል መሆኑንም መናገር ይቻላል።
በዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት ግንባታ የመደመር መንግስት ብቃትና ቁርጠኝነት በተለይም ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመሪነት አቅም የታየበት ነው። የመደመር መንግስት ቀደም ሲል የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በተቀመጠላቸው ጊዜ አጠናቆ ለአገልግሎት በማብቃት አዲስ የስራ ባህልና የመፈፀም አቅም አካብቷል።
በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው ተጓትቶ የቆየው የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ለዚህ ጥሩ ማሳያ መሆን ይችላል። በመሆኑም የመገጭ ፕሮጀክትን አጠናቆ ለስኬት በማብቃት የመደመር መንግስት የመፈፀም አቅሙን አሳይቷል።
የመገጭ የመስኖ ፕሮጀክቶች የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማጠናከርና የገበሬዎችን ገቢ ለማሳደግ እንዲሁም ለመጠጥ ውሃ የሚያገለግል ሰው ተኮር ፕሮጀክት በመሆኑ ግንባታው መጠናቀቁ ትልቅ ትርጉም አለው።
የዚህ ስራ ማሳያና መገለጫነቱ ተቋርጠው የነበሩና የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በሃላፊነትና በተጠያቂነት መርህ የማጠናቀቅ ጠንካራ አቋም መኖሩን ነው። በመሆኑም የመደመር መንግስት ከረጅም ዓመታት በፊት ተጀምረው የነበሩና አቅዶ የጀመራቸውን ፕሮጀክቶች በጥራትና በብቃት ማጠናቀቅ የሚችል መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል። ፕሮጀክቶችን መጀመር፣ ግንባታቸውን መከታተል፣ በተቀመጠው ጊዜ አጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃት የመደመር መንግስት ግልጽ አቋም ነው።
የፕሮጀክት አፈጻጸም ብቃት በተያዘለት ጊዜ፣ በተመደበለት በጀት፣ በተጠበቀው ጥራትና በሚያመጣው የልማት ጥቅም የሚለካ መሆኑ ይታወቃል። የዕቅድ ጥራት፣ የበጀት አጠቃቀም፣ የግዥና ኮንትራት አስተዳደር፣ የባለሙያዎች ብቃት፣ የግንባታ ጥራትና የቁጥጥር ሥርዓትም እንዲሁ። በእነዚህ ሁሉ መስፈርቶች የመደመር መንግስት በፕሮጀክት አፈፃፀም የተሳካለትና እየተሳካለት መሆኑን መናገር ይቻላል።
የከተሞች የኮሪደር ልማት፣ የቅርሶች እድሳት፣ የዘመናዊ ሪዞርት ግንባታዎችን በጥራትና በፍጥነት በማከናወን ለአገልግሎት አብቅቷል። ሌሎች ተጀምረው የተጠናቀቁና በግንባታ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችም በርካታ ናቸው። ከዚህ አንፃር የማዳበሪያ ፋብሪካና የቢሾፍቱ ኤርፖርት ግንባታ የመስራት አቅም ተጨማሪ ማሳያዎች እና የሀገር እድገት መሰረቶች ናቸው።
የማዳበሪያ ፋብሪካ መገንባት የግብርና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ በማዳበሪያ አቅርቦት ላይ የነበረውን የውጭ ገበያ ጥገኝነት ለመቀነስና የውጭ ምንዛሬ ወጪን ለማስቀረት የሚያስችል ነው። የአገር ውስጥ የኢንዱስትሪ አቅምን ለማሳደግም የሚያግዝ ይሆናል። በሌላ በኩል የቢሾፍቱ አየር ማረፊያ ፕሮጀክት ግንባታ የኢትዮጵያን የአቪዬሽን ዘርፍ እድገትና ማንሰራራት የሚያስቀጥል ታላቅ ፕሮጀክት ነው።
የመደመር መንግስት የፕሮጀክት አፈጻጸም አቅም ይበልጥ ሲጠናከርና ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት የሚበቁ ፕሮጀክቶች ቁጥር ሲጨምር የዜጎች ተጠቃሚነት ብሎም የሀገር እድገትና ማንሰራራት እየተጠናከረ ይሄዳል።