ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች እውን እንዲሆኑ የድርሻችንን እንወጣለን

አሶሳ፤ ጥቅምት 14/2019 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶች እውን እንዲሆኑ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።

ኢዜአ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያነጋገራቸው የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እንደገለጹት፣ የባህር በር  ጉዳይ ከማንኛውም የፖለቲካ ልዩነት በላይ የሆነ የህልውና ጉዳይ ነው።

የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረትና ብሔራዊ አጀንዳ መሆኑንም ያነሱት አመራሮቹ፣ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበርና የሕዝቦችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ (ቤህነን) ሊቀመንበር አቶ አብዱሰላም ሸንገል እንደተናገሩት፤ የባህር በር አጀንዳ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ያገናዘበ ህጋዊ መሰረት ያለው  ነው።

ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ጥያቄዋን ለማረጋገጥ የጀመረችው ጥረት በታሪክም ሆነ በዓለም አቀፍ ህግ ተቀባይነት ያለው በመሆኑ ለስኬቱ የሁሉም ዜጋ የጋራ ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል። 

ፓርቲያቸው በባህር በር ላይ ምንም አይነት የሀሳብ ልዩነት የለውም ያሉት ሊቀመንበሩ፤የተጀመረውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንደሚደግፉም አመልክተዋል።

የባሕር በር ባለቤትንት ጥያቄ  የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ያነሱት አቶ አብዱሰላም፣ ጥያቄው ከዳር እንዲደርስ የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።

በተመሳሳይ የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ለሜሳ ኔኖ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ባህር በሯን ያጣችው በወቅቱ በነበሩ ታሪካዊ ስህተቶች እንዲሁም በውስጣዊና ውጫዊ ተጽዕኖዎች መሆኑን አስታውሰዋል።

አሁን ላይ በታሪክ የራሷ የነበረውን የባህር በር በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ማስመለስ የምትችልበት ወቅት ላይ መሆኗን አንስተዋል።

የመደመር መንግስትና መላው ህዝብ በጉዳዩ ላይ የያዙት ጠንካራ አቋም የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህ አጋጣሚ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሀገራዊና ብሔራዊ አጀንዳዎች ላይ ያላቸውን የጋራ አቋም በተግባር የሚያሳዩበት መሆኑን ተናግረዋል።

መንግሥት ጉዳዩን በሰጥቶ መቀበል መርህና በቀጠናዊ ትብብር ለማሳካት የያዘው አቋምና እያደረገ ያለው ጥረት ፍትሐዊ መሆኑንና ይህም አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ እያገኘ መምጣቱን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት መረጋገጥ ለቀጣናው ሀገራት ጭምር አብሮ ማደግና ትሰስር ወሳኝ በመሆኑ የሚደረጉ ጥረቶች እንዲሳኩ ፓርቲው የበኩሉን ይወጣል ብለዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም