ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር አጀንዳዋ መነጠል አይቻልም - አምባሳደር ዘሪሁን አበበ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር አጀንዳዋ መነጠል አይቻልም - አምባሳደር ዘሪሁን አበበ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ)፦ ከታሪክ፣ ከመልክዓምድር፣ ከደህንነትና አሁን ካለችበት ቁመና አንፃር ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር አጀንዳ መነጠል እንደማይቻል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ
12ኛው የጣና ፎረም በውቢቷ ባሕር ዳር፣ በጣና ሐይቅ ዳርቻ “በአፍሪካ የሰላም መንገዶች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የጂኦ-ፖለቲካ ለውጥ” በሚል መሪ ሐሳብ ከዛሬ ጀምሮ እየተካሄደ ነው።
በዘንድሮው የጣና ፎረም በአፍሪካ አሕጉራዊ የሰላም መፍትሔ በማበጀት የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የጂኦ-ፖለቲካ ለውጥ ማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ይደረጋል።
በቀይ ባሕርና በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ደኅንነት ዙሪያ በምሥራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኞች የጣና ልዩ መልዕክተኞች ጉባኤ ተካሂዷል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ ፎረሙን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ከታሪክም ከጂኦግራፊም ይቀዳል ብለዋል።
ከታሪክ፣ ከመልክዓ ምድር፣ ከደኅንነት እና አሁን ካለችበት ቁመና አንጻር ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር አጀንዳ መነጠል እንደማይቻል ገልጸዋል።
በቀጣናው ያለው ነባራዊ ሁኔታ የኢትዮጵያን ተፈላጊነትና ትብብር የሚጠይቅ መሆኑንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በሰላም፣ በልማትና በጋራ ደኅንነት ላይ ተባብራ የመሥራት ፍላጎት እንዳላት ገልጸው፣ በጣና ፎረም በትብብር የማደግ ፍላጎቷን አንጸባርቃለች ብለዋል።
የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ መሆኑን ደጋግመን ተናግረናል ያሉት አምባሳደር ዘሪሁን፣ ለዚህ ስኬት የሚያግዙ የፖሊሲ ስልቶች መንደፏን ገልጸዋል።
ቀጣናው የሰላም፣ ዕድገትና መረጋጋት ጠባቂ መልህቅ እንደሚያስፈልገው ገልጸው፣ እሱም ዛሬም እንደ ትናንቱ ኢትዮጵያ ናት ብለዋል።