ቀጥታ፡

ባለአደራ አስተዳደሩ የትግራይ ክልልን ዘላቂ ሰላም እና ልማት ለማፋጠን የሚያደርጋቸውን ጥረቶች ለማሳካት የድርሻችንን እንወጣለን

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ)፦የትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር የክልሉን ዘላቂ ሰላም እና ልማት ለማፋጠን የሚያደርጋቸውን ጥረቶች ለማሳካት የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን ሲሉ ሜጀር ጀነራል ገብረ አድሃና ገለጹ።

የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት ሜጀር ጀነራል ገብረ አድሃና ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የትግራይ ክልል ሕዝብ የፕሪቶሪያ ስምምነት በተፈረመበት ወቅት በክልሉ ሰላም እንደሚሰፍን ትልቅ ተስፋ ሰንቆ እንደነበር ያነሳሉ።

ሕዝቡ ሰላምን ከመመኘት ባለፈ ለሰላሙ መጠበቅ የበኩሉን መስዋዕትነት ሲከፍል ቆይቷል ብለዋል።

ሆኖም የሕዝብና የሀገርን ሰላም የማይፈልገው ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን ከሌሎች ተመሳሳይ አቋም ካላቸው ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የኢትዮጵያ ሉአላዊ ሀገርነት እንዳይጠበቅ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።

የፌዴራል መንግሥት የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተከትሎ በትግራይ ክልል ሰላም እንዲሰፍን እያደረገ ላለው ያልተቋረጠ ጥረት አድናቆታቸውን የገለጹት ሜጀር ጄኔራል ገብረ አድሃና፣ ህገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን ግን ሰላም የማይገባው መሆኑን ተናግረዋል።

ቡድኑ ስምምነቱን ከማክበር ይልቅ የክልሉን ወጣቶች በማፈስ ለግጭት ለመጠቀም ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው፤ ለዚህ ዓላማው ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር የክህደት ተግባር ሲፈጽም መቆየቱን ገልጸዋል።

ሆኖም በፌዴራሉ መንግሥት ያላሰለሰ የሠላም ጥረት እና በሕዝቡ የሰላም ፍላጎት ምክንያት የህገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ከጠላት የተቀበለው የጥፋት ተልዕኮና የሸረበው ሴራ መክሸፉን ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ሕዝብ ለሰላምና ለልማት ያለውን ጽኑ ፍላጎት በማንሳትም፣ የፌዴራል መንግሥት የክልሉን ሰላምና መረጋጋት ለማጠናከር የትግራይ ክልል የፌዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር መመሥረቱ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

የባለአደራ አስተዳደሩ የሕዝቡን የሰላምና የልማት ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል አቅም እንዳለውም አንስተዋል።

ሕዝቡም ከአስተዳደሩ ጎን መቆሙን በማንሳት፣ ይህም በክልሉ ለዘላቂ ሰላምና ልማት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

አሁን ያለው ትልቁ ተግባር ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥና የልማት ሥራዎችን ማፋጠን ነው ብለዋል።

የባለአደራ አስተዳደሩ ከፌዴራል መንግሥት፣ ከክልሎችና ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመተባበር የክልሉን ሰላም ለማጠናከርና ልማትን ለማስፋፋት በትጋት መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የትግራይ ክልል ሕዝብ፣ ወጣቶች፣ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ እና ሌሎችም አካላት ከፌዴራል መንግሥትና ከባለአደራው አስተዳደር ጋር በጋራ እንዲቆሙ ጥሪ በማቅረብ፣ እሳቸውም እንደ አንድ ዜጋ ለክልሉ ሰላምና እድገት ተግተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

“ጽምዶ” የተባለው ጥምረት የእንቧይ ካብ የሆነና ሕዝባዊ ድጋፊ የሌለው ተራ ስብስብ ነው ሲሉም ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም