በኢትዮጵያ የዜጎች ጤና እና ስነ ተዋልዶ ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አስደናቂ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የዜጎች ጤና እና ስነ ተዋልዶ ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አስደናቂ ናቸው
ሀዋሳ፤ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የዜጎች ጤና እና ስነ ተዋልዶ ላይ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አስደናቂ ናቸው ሲሉ በተባበሩት መንግሥታት የስነ ሕዝብ ፈንድ (UNFPA) የኢትዮጵያ ተወካይ ኮፊ ኮዋሜ ገለጹ ።
በሲዳማ ክልል በመካሄድ ላይ ያሉት የእናቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች የተቀናጀ የስነ ተዋልዶ ጤና ሥራዎችን የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማትና ባለድርሻ አካላት ተመልክተዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የስነ ህዝብ ፈንድ (UNFPA) የኢትዮጵያ ተወካይ ኮፊ ኮዋሜ በምልከታቸው ማህበረሰቡ ጋር በመውረድ ጭምር የተሰሩ ጠንካራ የጤና ሥራዎችን ማየታቸውን ገልፀዋል።
በተለይም በእናቶችና ሕጻናት ጤና እንዲሁም በወጣቶች ስነ-ተዋልዶ ጤና ቅንጅታዊ ሥራዎች ላይ ከማህበረሰቡና ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በጋራ መክረው የበኩላቸውን እገዛ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የስነ ህዝብ ፈንድ (UNFPA) በኢትዮጵያ የሲዳማ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ፕሮግራሞች አስተባባሪ አቶ ታደሰ ሀይለማሪያም በበኩላቸው እንዳሉት፤ በእናቶችና ሴቶች ጤና እንዲሁም ወጣቶች ስነተዋልዶ ጤና ላይ በቅንጅት የሚሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት አምጥተዋል።
የሲዳማ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሰላማዊት መኩሪያ በበኩላቸው፤ በክልሉ ወጣቶች ጊዜያቸውን በአግባቡ ተጠቅመው ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ እንዲሆኑ የሚያግዙ ማዕከላት ተደራጅተዋል፡፡
በመንግሥትና በአጋር አካላት በተደራጁ 37 ማዕከላት ወጣቶችን በክህሎትና በዕውቀት የማብቃት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
በክልሉ በእናቶችና ሕጻናት ጤና አጠባበቅ እንዲሁም በስነተዋልዶ ጤና ላይ የሚሰሩ ሥራዎች በተቀናጀ መልኩ በመሰራታቸው ውጤት ተገኝቷል ያሉት ደግሞ የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ በላይነህ በቀለ ናቸው።
እናቶች በእርግዝና ወቅት በቂ ክትትልና የወሊድ አገልግሎት እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ የማሕጸን ጫፍ ካንሰርን ጨምሮ ሌሎች የቤተሰብ ዕቅድና የሕክምና አገልግሎቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።