የጎንደሩ መገጭ ግድብ በጋና የራሳችንን ስራ እንድንፈትሽ አነሳስቶናል - የጋናው ፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማህማ - ኢዜአ አማርኛ
የጎንደሩ መገጭ ግድብ በጋና የራሳችንን ስራ እንድንፈትሽ አነሳስቶናል - የጋናው ፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማህማ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ)፦ የመገጭ የመስኖ ግድብ በጋና በተመሳሳይ መልኩ ከብዙ ዓመታት በፊት ተጀምሮ ሳይጠናቀቅ የቀረውን ግድብ ዳግም ለመጀመር ጥንካሬ እና አቅም የሚሰጥ መሆኑን የሀገሪቷ ፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማህማ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክትን ዛሬ በይፋ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
በምርቃቱ ላይ የተገኙት የጋና ፕሬዝዳንት ጆን ድራማኒ ማህማ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተንበረከከች የአፍሪካውያን የነፃነትና የአልሸነፍ ባይነት ተምሳሌት መሆኗን አመልክተዋል።
የዚሁ ታላቅ ታሪክና ሥልጣኔ አካል የሆነችውን የጎንደር ከተማን የመጎብኘት የቆየ ምኞታቸው በመሳካቱም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ጋና ከሰሃራ በታች ነጻነቷን የተቀዳጀች የመጀመሪያ ሀገር መሆኗን አውስተው ከኢትዮጵያ ጋር በታሪክ እንደሚያገናኛት ተናግረዋል።
በጋና ዋና ወታደራዊ ሠፈር ውስጥ የሚገኘውና በታሪካዊው “የዲሴምበር 31 አብዮት” ወቅት የንቅናቄው ዋና ማዕከል ሆኖ ያገለገለው ወታደራዊ ምድብ "ጎንደር ባራክስ" ተብሎ እንደሚጠራ ጠቅሰዋል።
በዚህም ምክንያት የጎንደር ስም በጋናውያን ዘንድ ከጥንት ጀምሮ በጣም የታወቀና የተከበረ በመሆኑ፣ አህጉራዊ ታሪኳንና ሥልጣኔዋን በዓይናቸው ለማየት ሁልጊዜም ትልቅ መሻት እንደነበራቸው አውስተዋል።
የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት ታሪክን በተመለከተ ፕሬዚዳንቱ ሲናገሩ፣ የግድቡ ግንባታ እ.አ.አ በ1998 ሲጀመር እሳቸው ገና በወጣትነታቸው በምክትል ሚኒስትርነት የፖለቲካ ሕይወታቸውን የጀመሩበት ወቅት እንደነበር አውስተዋል።
ከዚያ በኋላ በሂደት የሀገራቸው ፕሬዚዳንት ለመሆን ቢበቁም፣ ፕሮጀክቱ ግን ለረጅም ዓመታት ሳይጠናቀቅ ተቋርጦ እንደነበር ገልጸዋል።
ሆኖም ከሶስት ዓመታት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት ፕሮጀክቱ ዳግም ህይወት ዘርቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ መጠናቀቁንና ለከተማዋ የመጠጥ ውሃና የመስኖ አገልግሎት የሚሰጠውን ቁልፍ በመጫን ሲያስመርቁ ማየታቸው ትልቅ ኩራት እንዲያድርባቸው ማድረጉን ተናግረዋል።
በጋና በተመሳሳይ መልኩ ከብዙ ዓመታት በፊት ተጀምሮ ሳይጠናቀቅ የተተወው የፑዋሉጉ (Pwalugu) የውሃና የመስኖ ፕሮጀክት እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የመገጭ ግድብ መሳካት የተቋረጠውን ፕሮጀክት ዳግም ለመጀመር ትልቅ ብርሃን እንደፈነጠቀና ጥንካሬ እንደሆናቸው ተናግረው ይህም አዲስ መነቃቃትን እንደፈጠረባቸውና የራሳቸውን ተመሳሳይ ስራ እንዲያከናውኑ እንዳነሳሳቸው ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንቱ የአህጉሪቱን መሪዎች ሚና በተመለከተ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የቀደሙት የአፍሪካ አባቶች አህጉሪቱን ከቅኝ ግዛት ነፃ ለማውጣት እንደታገሉ ሁሉ፣ የዛሬዎቹ መሪዎች ደግሞ ለሕዝቦቻቸው ኢኮኖሚያዊ እድገትንና ብልጽግናን ለማምጣት መትጋት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እያከናወኑ ያሉት ሥራ አፍሪካ የምትፈልገው ዓይነት ለውጥ አምጪ መሆኑን ገልጸው፣ ወደ ኢትዮጵያ በተመላለሱ ቁጥር ሀገሪቱ በየዓመቱ በአስደናቂ ሁኔታ እየተለወጠች እንደሆነ ለመመልከት መቻላቸውን አመልክተዋል።
በጎንደር እየተገነቡ ያሉ የቱሪዝም ሪዞርቶች ሲጠናቀቁም ለዕረፍት ዳግም ወደዚች ታሪካዊ ከተማ እንደሚመጡ ቃል በመግባት ለተደረገላቸው ወንድማዊ አቀባበል ምስጋናቸውን አቅርበዋል።