ቀጥታ፡

የአፍሪካን የኢኮኖሚ ነጻነት ለማረጋገጥ በራስ አቅም የሚካሄድ የምርምር አቅምን ማጎልበት ይገባል

ባህር ዳር፤ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ)፦‎የአፍሪካን የኢኮኖሚ ነጻነት ለማረጋገጥ በራስ አቅም የሚካሄድ የምርምር እና የጆርናል ህትመት አቅምን ማጎልበት እንደሚገባ የተለያዩ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች ገለጹ።

ከውጭ ጥገኝነት የተላቀቀ ችግር ፈች ምርምር በራስ አቅም ለማካሄድ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ተመላክቷል።

"እውቀትን ከመጠቀም ወደ ማመንጨት በመሸጋገር የአፍሪካን ቀጣይ ጉዞ በማስተካከል የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ የጣና ፎረም አካል የሆነውና የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች የተሳተፉበት ውይይት ዛሬ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተካሂዷል።


 

የአፍሪካ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ትብብር ጄኔራል ሴክሬታሪ ፕሮፌሰር ጆን ግያፖንግ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን እውቀት፣ ክህሎትና ጥበብ መፍታት ይገባል።

በዚህም የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ገበያውና ኢኮኖሚው የሚጠይቀውን የሰው ሃይል በብዛትና በጥራት ከማምረት ባሻገር ከውጭ ጥገኝነት የተላቀቀ ችግር ፈች ምርምር ለማካሄድ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

አሁን በዩኒቨርሲቲዎች የሚካሄደው ምርምር በውጭ አገራት የገንዘብ ድጋፍ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ጆን፣ የምርምሩ ግኝትም የድጋፍ አድራጊዎች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

ከውጭ ጥገኝነት የተላቀቀ ችግር ፈች ምርምር ለማካሄድ የአፍሪካ አገራት ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ምርምር ለማካሄድ የሚያስችል በቂ በጀት በየዓመቱ መመደብ እንዳለባቸው ጠቁመው፣ በዚህም ደቡብ አፍሪካ ጥሩ ተሞክሮ አላት ብለዋል።

በታንዛኒያ የዛንዚባር ስቴት ዩኒቨርሲቲ ቫይስ ቻንስለር ፕሮፌሰር ሰይድ አሊ ሃማድ በበኩላቸው እንዳሉት፤ አፍሪካውያን ከውጭ የገንዘብ ጥገኝነት የተላቀቀ የጆርናል ህትመት በማቋቋም ችግራቸውን በራሳቸው መፍታት አለባቸው።

በተለይም የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች እውቅትን፣ ክህሎትንና ሃብትን በማስተባበር የአህጉሪቱን ችግር የሚፈታ የምርምርና የጆርናል ህትመት ተቋም መገንባት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በዚህም በአህጉሪቱ ፈጣን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልማት እድገት በማስመዝገብ አፍሪካን የብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ግንኙነታቸውን በማጠናከር በአህጉሪቱ የኢኮኖሚ ነጻነትን ለማረጋገጥ የሚሰራውን ሥራ በምርምር ማገዝ አለባቸው ያሉት ደግሞ የሃርጌሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አህመድ (ዶ/ር) ናቸው።


 

ለዚህም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የምርምርና የጆርናል ህትመት ተቋም በመመስረት በራስ አቅም እውቀትን ከማመንጨት ባለፈ ለአህጉሪቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ መስራት ይገባል ብለዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፤ የአፍሪካን ኢንዱስትሪ፣ ቴክኖሎጂ እና የሰው ሃይል አቅም ለማሳደግ ቅንጅታዊ አሰራርን ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

ከጣና ፎረም ጎን ለጎን እየተካሄደ ያለውን የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የፕሬዚዳንቶች ውይይትን በማጠናከር የአህጉሪቱን እድገት ማፋጠንና ችግሮችን መፍታት ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው ውይይት ላይ ከአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በተጨማሪ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ወጣት ምሁራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ተሳትፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም