የሽግግር ፍትሕ የመደመር መንግሥት የመብት ጥሰቶችን በሕግ ሥርዓት መፍትሔ ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እርምጃ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሽግግር ፍትሕ የመደመር መንግሥት የመብት ጥሰቶችን በሕግ ሥርዓት መፍትሔ ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እርምጃ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ)፦ የሽግግር ፍትሕ አካታችና የተሟላ ሂደት የመደመር መንግሥት የዘመናት ቁርሾና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሕግ ሥርዓት መፍትሔ ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እርምጃ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስትር ሐና አርዓያስላሴ ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ
የፍትሕ ሚኒስቴር እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሽግግር ፍትሕ የጋራ ፎረም ምስረታ መርሃ ግብር አካሂደዋል።
የፍትሕ ሚኒስትር ሐና አርዓያስላሴ በዚህ ወቅት፤ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን ለማዘጋጀት ከረዥም ጊዜ ጀምሮ የጥናትና የምክክር ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
በዚህም በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በርካታ መድረኮች መካሄዳቸውንና ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሐሳቦች መሰብሰባቸውን አንስተዋል።
ፖሊሲው በመንግሥት ምክር ቤት ከጸደቀ በኋላ ለተግባራዊነቱ የሚያስፈልጉ ሕጋዊ ማዕቀፎችን የማዘጋጀት ሥራ መከናወኑን ጠቁመዋል።
የሽግግር ፍትሕ ሂደትም በግጭቶች ምክንያት የተፈጠሩ ቁርሾዎችን ለመፍታት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዳግም እንዳይፈጸሙ ለመከላከልና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።
የመደመር መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥበቃን በማጠናከር ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን ለማጽናትና የሕግ-የበላይነትን ለማስፋት ውጤታማ እርምጃዎችን ወስዷል ብለዋል።
በዚህም የፍትሕ ተቋማትን የመፈጸም አቅም ለማጎልበት የተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎችና የአሠራር ሥርዓቶች ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የሽግግር ፍትሕ አካታችና የተሟላ ሂደትም የመደመር መንግሥት የዘመናት ቁርሾና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሕግ ሥርዓት መፍትሔ ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ተጨባጭ እርምጃ መሆኑን አስረድተዋል።
የሽግግር ፍትሕ የጋራ ፎረም ምስረታም የሂደቱን የቅድመ ዝግጅትና የዝግጅት ምዕራፍን ወደ ትግበራ ለመቀየር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ምክረ ሐሳቦችም የሽግግር ፍትሕ ትግበራ አንዱና ወሳኙ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
በምክክሩ በቀረቡ የሕዝብ ምክረ ሐሳቦች መሠረትም የኢትዮጵያን ዘላቂ የሰላም ግንባታና የሕግ የበላይነት በሚያጠናክር መልኩ የሽግግር ፍትሕ እንደሚተገበር አንስተዋል።
የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲና ተቋማትን በማቋቋም ተግባራዊ አፈጻጸም ሂደት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን ቢራቱ በበኩላቸው፤ የሽግግር ፍትሕ ትግበራን ውጤታማነት ለማሳደግ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የጋራ ፎረሙም በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ የዜጎችን ግንዛቤን በማሳደግ ለተቋማዊ ለውጦች የሚያግዙ ምክረ ሐሳቦችን ለማቅረብ የሚያግዝ ቋሚና የጋራ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አሕመድ ሁሴን በበኩላቸው፤ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ያለፉ በደሎችን በመመርመር እውነትን ከማውጣትና ለተጎጂዎች ፍትሕ ከማረጋገጥ ባለፈ ለእርቅ፣ ዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ መግባባት መሠረት የሚጥል ሂደት መሆኑን ገልጸዋል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከሕብረተሰቡ ጋር በቅርበት የሚሠሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።