የምሥራቅ አፍሪካን የቀይ ባሕር ደኅንነት ለማስጠበቅ የቀጣናውን ሀገራት አስተማማኝ አጋርነት ማጎልበት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የምሥራቅ አፍሪካን የቀይ ባሕር ደኅንነት ለማስጠበቅ የቀጣናውን ሀገራት አስተማማኝ አጋርነት ማጎልበት ይገባል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ)፦ የምሥራቅ አፍሪካን የቀይ ባሕር ደኅንነት ለማስጠበቅ የቀጣናውን ሀገራት አስተማማኝ አጋርነት ማጎልበት እንደሚገባ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ
12ኛው የጣና ፎረም በውቢቷ ባህርዳር በጣና ሐይቅ ዳርቻ "በአፍሪካ የሰላም መንገዶች የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የጂኦ-ፖለቲካ ለውጥ" በሚል መሪ ሃሳብ ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል።
በዘንድሮው የጣና ፎረም በአፍሪካ አሕጉራዊ የሰላም መፍትሔ በማበጀት የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የጂኦ-ፖለቲካ ለውጥ ማምጣት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ይደረጋል።
አፍሪካን ከእውነት ተቀባይነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገር አሕጉራዊ ከፍተኛ ተቋማት በሚኖራቸው ሚና ላይ ይመክራል።
በመርሃ ግብሩም በቀይ ባሕርና ምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ደኅንነት ዙሪያ በምሥራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኞች የጣና ልዩ መልዕክተኞች ጉባኤ ይካሄዳል።
በመድረኩም በአፍሪካ ዘላቂ ሰላም፣ የአየር ንብረት ለውጥና የማይበገር ማኅበረሰብ መገንባት በሚያስችሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የጎንዮሽ ውይይት መካሄድ ጀምሯል።
ሕገ-ወጥ ኢኮኖሚ በደቡብ ሱዳንና ሱዳን ግጭት የሚደረግ የገንዘብ እንቅስቃሴ፣ የአፍሪካ ኤጀንሲዎች በዓለም አቀፍ ተቋማት ለውጥ ላይ ድጋፍ ማሰባሰብ፣ በአፍሪካ ዘላቂ ሰላም በማስፈን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕጎችን ማስከበር፣ ቀጣናዊ ንግድና ሰላም ሌሎች የጎንዮሽ ምክክር የሚደረግባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በዚህ መድረክ እንደገለጹት፤ የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ-ፖለቲካና ውስብስብነት እየተባባሰ መጥቷል።
የአፍሪካ ቀንድ በነዳጅ፣ ወሳኝ ማዕድናት፣ ያልታረሰ መሬትና ውሃን ጨምሮ ያልተነኩ የተፈጥሮ ሀብቶች ያሉበት ቀጣና መሆኑን ገልጸዋል።
ቀጣናው ዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች የሆኑት የቀይ ባሕር፣ የዓረብ ምድር፣ የሕንድ ውቅያኖስና የሜዲትራኒያን ባሕርን የሚያገናኝበት ስትራቴጂክና ወሳኝ መስመር መሆኑንም ተናግረዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ-ፖለቲካዊ ሁኔታ ታሪካዊ በደሎች፣ የሀብት ውዝግብና ውስብስብ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ውጥረቶች ያሉበት መሆኑን አስረድተዋል።
በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣናም ጽንፈኝነትና ሽብርተኝነት የማያቋርጥ ስጋት ፈጥረዋል ብለዋል።
በዚህ ውስብስብ ቀጣናም በቀይ ባሕር ላይ እየጨመረ የመጣው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለቀጣናው ሀገራት ስጋት መሆኑን ገልጸዋል።
በባብኤል መንደብና በሰፊው ቀይ ባሕር ውስጥ በንግድ መርከቦች ላይ እንደ አዲስ የተከፈቱ ጥቃቶች መኖራቸውን በመጠቆም፤ እነዚህ ክስተቶች በደጃፋችን ላይ የሚከናወኑ ለውጦች ናቸው ብለዋል።
እነዚህ ክስተቶች የቀይ ባሕር ደኅንነት በጥቂት የባሕር ዳርቻ ሀገራት ጥበቃና ባለቤትነት ላይ ብቻ ሊተው እንደማይችል ማሳያዎች መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
በመሆኑም የቀጣናውን ደኅንነትና መረጋጋት ለማስጠበቅና የወደፊቱን ለመቅረጽ የቀይ ባሕር ዳርቻ ሀገራት ብቻ ሳይሆን በቀጣናው ሀገራት መካከል በአስተማማኝ አጋርነትና ትብብር መፍጠር ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር ንግድ ሙሉ በሙሉ በቀይ ባሕር የተመረኮዘና የቀጣናው መሠረት መሆኗን ጠቅሰው፤ የደኅንነት ስጋቷን የማስወገድ፣ የባሕር ንግዷንና የንግድ መርከቦቿን መጠበቅ ግዴታ እንዳለባት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ለማስመዝገብ፣ ጠንካራ ቀጣናዊ ውህደት ለማምጣት በትኩረት እየሠራች መሆኑን አስታውቀዋል።
የቀጣናው ተለዋዋጭ ጂኦ-ፖለቲካዊ ሁኔታ የሚፈጠሩትን ውስብስብ ፈተናዎች ለመሻገር ፈጠራና አካታች ስልቶችን መከተል እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።