ቀጥታ፡

 በክልሉ በዲጂታል ኢኒሼቲቭ ንቅናቄ መፍትሔ አፍላቂ የሰው ኃይል ለመገንባት ትኩረት ተደርጓል

ደብረማርቆስ ፤ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ)፦‎ በአማራ ክልል በዲጂታል ኢኒሼቲቭ ንቅናቄ መፍትሔ አፍላቂ የሰው ኃይል ለመገንባት ትኩረት መደረጉን የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የዲጂታል ኢኒሼቲቭ የንቅናቄ መድረክ በደብረ ማርቆስ ከተማ ዛሬ አካሂዷል።


 

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አማረ አለሙ በመድረኩ እንዳሉት፣ በኢኒሼቲቩ መፍትሔ አፍላቂ የሰው ኃብት በመገንባት ዕውቀትና ክህሎትን ማስታጠቅ ያስፈልጋል።

ለዚህም ዜጎች የቴክኖሎጂ ዕውቀታቸውን በማሳደግ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩበትን፣ የመረጃ አያያዝና አገልግሎቶችን በዘመናዊ መንገድ የሚያገኙበትን አቅም ለመፍጠር እየተሠራ ነው ብለዋል።

ለአብነትም በበጀት ዓመቱ ከ900 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች የዲጂታል ክህሎት ሥልጠና ለመስጠት ታቅዶ፣ በሩብ ዓመቱ ከ6 ሺህ በላይ ሠልጥነው ሰርተፍኬት መውሰዳቸውን አስረድተዋል።


 

የክልሉ የከተማ ክላስተር ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መሐመድ ጀማል (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ኢንሼቲቩ ለወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የዲጂታል መሠረተ ልማትና የሰው ኃብት ልማትን በማሳደግም ለክልሉ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲያበረክት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ ቴክኖሎጂውን ተደራሽ በማድረግ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለተቀላጠፈ የአገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ ለማዋል በቅንጅት እየተሠራ ነው ብለዋል።

ኢኒሼቲቩን ከሥራ ዕድል ፈጠራ ባሻገር፣ በርካታ ተቋማት ሥራቸውን ወደ ዲጂታል እንዲቀይሩ እንቅስቃሴ መጀመሩን የገለጹት ደግሞ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አበበ ጓዱ ናቸው።


 

የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በሁሉም ወረዳዎች ሥራ ለማስጀመር ከ391 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በንቅናቄ መድረኩ የአዊ፣ የምዕራብ፣ የምሥራቅና የሰሜን ጎጃም እንዲሁም የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሥራና ክህሎት ባለሙያዎችና አጋር አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም