ቀጥታ፡

የልማት ስራዎችን አጠናክረን እናስቀጥላለን -የካፋ ዞን ነዋሪዎች

ቦንጋ ፤ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ)፦‎ በአካባቢያቸው በመንግስት ለሚከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ስኬታማነት ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የካፋ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን በበኩላቸው ከህዝቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ እንደሚሰጥ  አስታውቀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከካፋ ዞን ከተውጣጡ የማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር "ማንሰራራት ለክልላችን ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ በቦንጋ ከተማ ውይይት አካሂደዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ሻወራሻ ብርሃኑ ሀይሌ እና መምህርት ጥሩነሽ ወንድአፍራሽ በሰጡት አስተያየት የመደመር መንግሥት ባለፉት ዓመታት የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ በርካታ ተግባራት አከናውኗል።


 

በዚህም በትምህርት፣ በጤና ፣ በመሰረተ ልማት እንዲሁም በሌሎችም ዘርፎች ማህበረሰቡን በማሳተፍ በተሰራው ስራ ሕብረተሰቡ ተጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይሁንና በአካባቢው ተጀምረው የተጓተቱ የመንገድ ፣ የውሃ፣ የድልድይ ግንባታና ጥገና ስራዎች መኖራቸውን ጠቅሰው የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ከዳር እንዲደርሱ ተሳትፎዋቸውን እንደሚያጠናክሩ አመላክተዋል ።

በጤና ተቋማት የሚስተዋሉ የአገልግሎት ክፍተቶችን እንዲሁም የኑሮ ውድነትን ለሚያቃልሉ ተግባራት ትኩረት እንዲሰጥም ጠይቀዋል ።

ወጣቱን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ በከተማና በገጠር በተሰሩ ስራዎች በርካቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን ያነሱት ደግሞ ወጣት አእላፍ ለማና መንግስቱ ሀይሌ ናቸው።

ይሁንና ካለው ፍላጎት አንጻር በቂ ባለመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል።


 

መንግስት በየዘርፉ ለሚያከናውናቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ስኬታማነት የበኩላቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን ከህብረተሰቡ የተነሱ ሀሳቦች ለክልሉ ልማት ተጨማሪ አቅም መሆናቸውን ተናግረዋል።

የህብረተሰቡን አቅም በተደመረ መንገድ በማጠናከር  የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል።


 

ባለፉት ኣመታት የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት በተሰጠው ትኩረት በየዘርፉ በርካታ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አንስተዋል።

እያደገ የመጣውን የሕዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ የሕዝቡን አቅም በመደመር በተቀናጀ አግባብ  ጥረት እንደሚደረግ አመላክተዋል።

የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በጥራት እንዲጠናቀቁ ጠንካራ የክትትልና የቁጥጥር ስራ እንደሚሰራ ጠቅሰው፣ ከመልካም አስተዳደር አንፃር የሚነሱ ብልሹ አሰራሮችን ለመፍታት የክልሉ መንግሥት በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም