ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ10 ምሁራንን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ እድገት አጸደቀ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድ የ10 ምሁራንን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ደረጃ እድገት አፅድቋል።

ቦርዱ ውሳኔውን ያሳለፈው ትናንት ባደረገው ስብስባ ነው።

ይህ እድገት ምሁራኑ በትምህርትና አካዳሚያዊ አገልግሎት፣ በምርምር እና በማኅበረሰብ አገልግሎት ያስመዘገቧቸውን የላቀ ውጤቶችና አስተዋፅዖዎች መሠረት ያደረገ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።

በዚሁ መሰረት ዶ/ር አብርሃም ገብሬ ተካለኝ በስትራክቸራል ኢንጂነሪንግ፣ ዶ/ር አዳነ ቢተው ተገኘ በሜዲካል ማይክሮባዮሎጂ፣ ዶ/ር አደይ ፈለቀ ደስታ በኢንቫይሮሜንታል ማይክሮባዮሎጂ፣ ዶ/ር ደሳለኝ ያየህ አያል በዲሳስተር ሪስክ ማኔጂሜንት፣ ዶ/ር ኃይለልዑል ንጉሴ ዱባለ በቨተርነሪ ኢፒዲሞሎጂ፣ ዶ/ር ካሳ ሚካኤል ወ/የሱስ በማቲማቲክስ ኢጁኬሽን፣ ዶ/ር ሰለሞን ገነት ገብሬ በባዮኬሚስትሪ፣ ዶ/ር ሰለሞን አረዓያ ካሳ በጀነራል ኢዱኬሽን፣ ዶ/ር ያረጋል አሳቤ ላቀ በአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ እንዲሁም ዶ/ር የድልፋና ሰጠአርጌ መኮንን በፊዚካል ኬሚስትሪ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል።

ይህ ስኬት ዩኒቨርሲቲው ለአካዳሚያዊ ልህቀት፣ ለምርምርና ፈጠራ እንዲሁም ለማኅበረሰብ አገልግሎት ያበረከተውንና እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ማሳያ ተደርጎ እንደሚወሰድ ተመላክቷል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለዚህ ከፍተኛው የአካዳሚክ ማዕረግ ለበቃችሁ ምሁራን እንኳን ደስ አላችሁ ያለ ሲሆን በቀጣይ የተጀመረውን የአካዳሚክ፣ ምርምርና አገልግሎት ልቀት ለማምጣት እንዲተጉ ዩኒቨርሲቲው ጥሪውን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም