የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ያለበት የሕልውና ጉዳይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ያለበት የሕልውና ጉዳይ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ ሕጋዊና ተፈጥሯዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ያለበት የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ በሁሉም መስክ ተጠናክሮ ሊሠራበት እንደሚገባ ተገለጸ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ
በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ከቀይ ባሕር ቀጣና በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት የምትገኘው ኢትዮጵያ የገናና ታሪክ ሥልጣኔና ማንነቷ ከባሕር በር ባለቤትነቷ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ነው።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የሀገር ውስጥ ባንዳን በመጠቀም ከሦስት አሥርት ዓመታት በፊት የመግቢያና መውጫ በሮቿን በማስዘጋት ሀገርን የባሕር በር አልባ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ ሕጋዊ፣ መልክዓ ምድራዊና ተፈጥሯዊ የባሕር በር መገለልም በኢኮኖሚ ዕድገት፣ ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳትን እያስከተለ ይገኛል።
የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ በሰላማዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ሰጥቶ መቀበል መርህ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ቅቡልነት እንዲያገኝ ተደርጓል።
በዚህም ሰላማዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ሰጥቶ መቀበል መርህን የተከተለው የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ አሁን ላይ እንዴት ይፈጸም፣ እንዴትስ ምላሽ ያግኝ ወደሚል ወሳኝ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
የመከላከያ ሰራዊት የቀድሞ አባል ብርጋዴር ጀነራል ካሣ ወልደሰማዕት ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ከገናና የሥልጣኔ ታሪክና ማንነቷ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ነው።
ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የነበራትን የባሕር በር ያጣችበት መንገድ ሕጋዊ መሠረት የሌለውና ሀገርን ለማዳከም የተወጠነ ኢ-ፍትሐዊ ሴራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ከባሕር በር ባለቤትነት መገለሏም የሕዝብ ውክልና የተሰጠው መንግሥትም ሆነ የሕግ አደረጃጀት እንደሌለ አስታውሰዋል።
የሀገር ውስጥ ባንዳና ባዕድ ኃይሎች በፈጠሩት ጥምረት ኢትዮጵያ ለሺህ ዘመናት ከናኘችበት የቀይ ባሕር ቀጣና እንድትገለል በማድረግ ጉልህ የኢኮኖሚ ጉዳት እየደረሰባት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከባሕር በር ባለቤትነት መገለሏም ቀጣናዊ የሽብር ኃይሎችን እና የባሕር ላይ ውንብድናን ለመዋጋት የሚጠበቅባትን ሚና እንደገደበው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥርና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትም አስተማማኝ የባሕር መውጫና መግቢያ በር ሊያገኝ የሚገባው የሕልውና ጉዳይ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።
የባሕር በር ባለቤትነት ዲፕሎማሲያዊ ጥያቄም ምላሽ ሊሰጠው የሚገባ ፍትሐዊና ምክንያታዊ አጀንዳ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።
አምባሳደር ቶፊቅ አብዱላሂ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን የባሕር በር በማሳጣት በቀይ ባሕር ቀጣና የሚኖራትን ተፅዕኖ ለመገደብ ያልተሸረበ ሴራ አልነበረም ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም በግብፅ ፊት አውራሪነት የኢትዮጵያን ፍትሐዊና ምክንያታዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለማሳነስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የመደመር መንግሥት ውጤታማ የዲፕሎማሲ ሥራም የግብፅን ሴራ በመበጣጠስ ታሪካዊ፣ ሕጋዊና ምክንያታዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄን ዓለም እንዲገነዘብ ማስቻሉን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ከዓባይና ቀይ ባሕር መነጠል አይቻልም ያሉት አምባሳደር ቶፊቅ፤ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በዓባይ ወንዝ እውን እንደሆነ ሁሉ፤ የባሕር በር ባለቤትነትን ማረጋገጥም የሕልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የፌዴራል ሕግና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዘካርያስ ኤርኮላ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ በዓለም አቀፍ ሕግ ተቀባይነት አለው ብለዋል።
ለዓመታት ተዳፍኖ የኖረው የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ መነሳቱም የኢኮኖሚ ዕድገትን፣ የሕዝብ ቁጥርንና ቀጣናዊ ደኅንነት ስጋትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ የባሕር በር ባለቤትነት የሁሉም ዜጎች የጋራ ጥያቄና የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ተዘግቶባት ልትኖር አትችልም ያሉት ዘካርያስ ኤርኮላ (ዶ/ር)፤ ምክንያታዊና ፍትሐዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም ምላሽ ማግኘት ያለበት የሕልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።