ቀጥታ፡

ለ19 ዓመታት ግንባታው የቆየውን የመገጭ የመስኖ ፕሮጀክት በመደመር እሳቤ ከእርግማን ወደ ታላቅ በረከት ለውጠናል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ)፦ለ19 ዓመታት ግንባታው የቆየውን የመገጭ የመስኖ ፕሮጀክት በመደመር እሳቤ ከእርግማን ወደ ታላቅ በረከት መለወጡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክትን ዛሬ በይፋ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምርቃቱ ወቅት እንዳሉት የመገጭ ፕሮጀክት 19 ዓመታትን እንደቆየና ይህም ከደካማ የመፈጸምና ፕሮጀክት የመምራት አቅም የሚመነጭ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እምቅ ሀብቶች ቢኖሯትም ወደ ተደራጀ አቅም መቀየር ሳትችል መቆየቷ እንደ መገጭ ያሉ ፕሮጀክቶች እንዲዘገዩ ማድረጉን አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁለት ዓመት በፊት ፕሮጀክቱን በጎበኙበት ወቅት ግንባታው ባለቤት አልባ እና ደካማ የፕሮጀክት አፈጻጸም እንደነበረው መመልከታቸውን አውስተዋል።

ይህም የጎንደር ህዝብ ውሃ እንዲጠማና በእምቅ ሀብቱ ተጠቃሚ መሆን ሳይችል መቆየቱን ተናግረዋል።

የመደመር መንግስት ፕሮጀክቱን በመገምገም ግድቡ ባለቤት እንዲኖረው በማድረግ፣ ተቋራጭ በመቀየር እና የቅርብ ክትትል በማድረግ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ማድረጉን ነው የገለጹት።

ለ19 ዓመታት ፕሮጀክት ማዘግየት እርግማን እና ጥፋት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመደመር እሳቤ እርግማንን ወደ ታላቅ በረከት መቀየር መቻሉን አመልክተዋል።

ሉዓላዊ አቅም አለመገንባት፣ ጨርሶ አለመጀመር እና ጀምሮ አለመከወን እንዲሁም በፌደራል እና ክልል መንግስታት በኩል ስርዓታዊ ስሉጥነት አለመኖሩ በፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ የሚታዩ ስብራቶች መሆናቸውን አንስተዋል።


 

መንግስት እነዚህ ስብራቶች በመጠገን የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም እና በተያዘላቸው ጊዜ የማጠናቀቅ አቅም መገንባቱን አመልክተዋል።

ጎንደር እንደ መገጭ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች ይገባታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ ከተማዋን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በታሪካዊቷ ጎንደር የቱሪዝም መዳረሻነቷን የሚያሳድጉ ስራዎች እንደሚከናወኑም ጠቁመዋል።

የጎንደር ህዝብ ለልማት አንድ ላይ መቆም እና የልማት ስራዎችን መጠበቅ እንደሚገባው አሳስበዋል።

መንግስት የአማራ ክልል የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

የመደመር መንግስት የኢትዮጵያን ስልጣኔ እውን ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝና ለዚህ ታላቅ ራዕይ መሳካት ሁሉም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም