በአምቦ ከተማ የመሬት አስተዳደር በዲጅታል የታገዘ አገልግሎት መስጠቱ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንድናገኝ አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በአምቦ ከተማ የመሬት አስተዳደር በዲጅታል የታገዘ አገልግሎት መስጠቱ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንድናገኝ አስችሏል
አምቦ፣ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በአምቦ ከተማ የመሬት አስተዳደር በዲጂታል የታገዘ አገልግሎት መስጠቱ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንድናገኝ አስችሎናል ሲሉ ተገልጋዮች ተናገሩ።
የኢዜአ ሪፖርተር በአምቦ ከተማ አስተዳደር የመሬት አስተዳደር ቢሮ በመገኘት የአገልገሎት አሰጣጡን በተመለከተ በመቃኘት ተገልጋዮችንም አነጋግሯል።
በእለቱ አገልግሎት ፈልገው የመጡ ደንበኞችም የአገልግሎት አሰጣጡ ዲጅታል ከተደረገ በኋላ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እያገኘን ነው ብለዋል።
ከተገልጋዮቹ መካከል አቶ ጥበበ ይማነ፤ ከዚህ ቀደም ከመኖሪያ ቤት ባለቤትነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንታት ይወስድ እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን በአጭር ግዜ ውስጥ እየተገለገልን ነው ብለዋል።
በከተማዋ የተጀመረው የዲጅታል አገልግሎት አሰጣጥ ጊዜ እና ጉልበትን እንዲሁም ገንዘብን የሚቆጥብ ምርጥ አሰራር መሆኑን ተናግረው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ሌላኛው ተገልጋይ አቶ ብርሃኑ ተስፋዬ፤ የመሬት ካርታ ለማግኘት ወደ ጽሕፈት ቤቱ መምጣታቸውን ገልጸው በፍጥነት ተስተናግደው ያጠናቀቁ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት አገልግሎቶችን የማግኘት ጉዳይ አሰልቺ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ዘመናዊና ቀልጣፋ አሰራር በመዘርጋቱ አመስግነዋል።
በከተማዋ የመሬት አስተዳደር የካዳስተር ምዝገባ አገልግሎት ለማግኘት የመጡት ወይዘሮ ወይንሸት አቶምሳ፤ በቴክኖሎጂ የተደገፈው የመሬት አገልግሎት ከዚህ ቀደም የነበረውን እንግልት አስቀርቷል ብለዋል።
በመሆኑም አገልግሎቱን እየሰጡ ላሉት ባለሙያዎች ምስጋና በማቅረብ መሰል የአገልግሎት አሰጣጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
በአምቦ ከተማ የመሬት አስተዳደር የካዳስተር ምዝገባ ባለሙያ መልካ አረጋ፤ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ሥርዓቱ የከተማዋን የመሬት ሀብት በአግባቡ ከማስተዳደር ባለፈ ለተገልጋዮች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
አሰራሩ የመሬት መረጃዎችን በዘመናዊ መንገድ ለመመዝገብና ለመቆጣጠር በማስቻሉ ከዘርፉ ጋር የተያያዙ የመሬት ምዝበራና ወረራንም አስቀርቷል ብለዋል።
በአምቦ ከተማ አስተዳደር ከ11 ሺህ በላይ ዜጎች በዘመናዊው ሥርዓት ተመዝግበው የመሬት ባለቤትነት ካርታ የወሰዱ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።