የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከብሄራዊ ጥቅም ባለፈ ለቀጣናዊ ትስስር ጠንካራ መሰረት የሚያኖር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከብሄራዊ ጥቅም ባለፈ ለቀጣናዊ ትስስር ጠንካራ መሰረት የሚያኖር ነው
ጅማ፣ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከብሄራዊ ጥቅም ባለፈ ለቀጣናዊ ትስስር ጠንካራ መሰረት የሚያኖር መሆኑን የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
ትልቅ አገር፣ ትልቅ ህዝብ፣ ታላቅ ርዕይ
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በታሪክ፣ በመልክአ ምድርም ይሁን በዓለም አቀፍ ህግ ተቀባይነት ያለው መሆኑ ይታወቃል።
በመሆኑም የትውልድ ጥያቄ የሆነው የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ በሰጥቶ መቀበል መርህ ምላሽ እንዲያገኝ የዲፕሎማሲ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጅማ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከብሄራዊ ጥቅም ባለፈ ለቀጣናዊ ትስስር ጠንካራ መሰረት የሚያኖር መሆኑን ገልጸዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሃይድሮሊክና የውሃ ሀብት ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዳውድ ተማም (ዶ/ር)፣ ቀይ ባህር የዓለም አቀፍ ንግድ ወሳኝ መስመር በመሆኑ ኢትዮጵያም በዚሁ ባህር ላይ መውጫና መግቢያ በር ሊኖራት የግድ መሆኑን አንስተዋል።
የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ከንግድም ባለፈ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ የትውልዱ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የሁላችንም ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የዓለም አቀፍ የንግድ ትስስሯን ለማስፋትና በቀጣናው ያላትን ስትራቴጂካዊ ተሳትፎ ለማሳደግም ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ጌታቸው ጥላሁን (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ማጣት ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ብዙ ዋጋ ያስከፈላት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከአባይ እና ከቀይ ባህር ተነጥላ መኖር የማትችል መሆኑን በማንሳት የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄዋ በትውልዱ ጥረት በድፕሎማሲያዊ ጥረት ምላሽ ማግኘት ይኖርበታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ከራሷም ባለፈ ለቀጣናዊ የንግድ ትስስር፣ ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።