ቀጥታ፡

ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያለን ክብርና ምስጋና የላቀ ነው

ደብረ ማርቆስ፤ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ) ፡-ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያለን ክብርና ምስጋና የላቀ ነው ሲሉ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ቀን  የሠራዊቱን ዘመናዊ አደረጃጀትና ታሪካዊ ጉዞ ከማስታወስ ባለፈ፣ ለሀገር ሉዓላዊነትና ለሕዝብ ሰላም ሲባል የተከፈለውንና እየተከፈለ ያለውን ሕያው መስዋዕትነት ለመዘከርና እውቅና ለመስጠት የሚከበር ነው። 

እለቱ በየዓመቱ ጥቅምት 15 ቀን በተለያዩ ስነ ስርአቶች በድምቀት ይከበራል።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸው ክብርና ምስጋና ከፍተኛ ምሆኑን ገልጸዋል ።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ቀን መከበሩም ሰራዊቱ  ለሀገር መጽናት  እየከፈለ ያለውን ዋጋ አጉልቶ የሚያሳይ  መሆኑን ተናግረዋል ።

በደብረ ማርቆስ ከተማ የቀበሌ 02 ነዋሪ አቶ በቀለ መንግስት እንደገለጹት ሠራዊቱ ለሀገር ሉአላዊነት መከበርና ለሰላም መስፈን  እየከፈለ ያለው መስዋዕትነት የህዝብ አለኝታና መከታነቱን የሚያሳይ ነው።

ለዚህ ተግባሩም ከፍተኛ ክብርና ምስጋና የሚቸረው መሆኑን ተናግረዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ቀን መከበሩም ሰራዊቱ  ለሀገር ሉአላዊነት መከበር እየከፈለ ያለውን መስዋእትነት የሚዘክር በመሆኑ ትልቅ ግምት የሚሰጠውና በጉጉት የሚጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በከተማው የቀበሌ 07 ነዋሪ አቶ ጌታሁን አራጋው በበኩላቸው መከላከያ ሰራዊት ለሀገር ክብርና ሉአላዊነት መከበር ህይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑን ተናግረዋል።

የመከላከያ ሰራዊት ቀን ለሀገር ሉአላዊነት የሚከፈል መስዋትነትና የፍቅር መገለጫ መሆኑን አመልክተዋል።

እለቱ ሰራዊቱ ለሚከፍለው መስዋትነት እውቅና ከመስጠቱ ባሻገር ዜጎች  የሀገር ፍቅርን አጥብቀው እንዲገነዘቡ በማድረግ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል ።


 

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ማክዳ ሞላ በበኩሏ የመከላከያ ሰራዊት ቀን መከበር ወጣቶቱ ለሀገር የሚከፈል ዋጋን ይብልጥ የሚረዳበት መሆኑን አመልክታለች ።

መከላከያ ሰራዊት ለሀገርና ለህዝብ እየከፈለ ላለው መስዋእትነት ላቅ ያለ ክብር እንዳላት ገልጻለች።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም