ቀጥታ፡

የህዝብን የልማት ጥያቄዎች በመመለስ የዜጎችን ሕይወት የማሻሻል ሥራ ይጠናከራል- ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) 

ዱራሜ፣ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ)፡-የህዝብን የልማት ጥያቄዎች በፍጥነት በመመለስ የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል የሚከናወኑ ተግባራት በቀጣይም ይጠናከራሉ ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ገለጹ።

የመደመር መንግሥት ህብረተሰብ አቀፍ የምክክር መድረክ ዛሬ በከምባታ ዞን ዱራሜ ከተማ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) በክልሉ ያሉ የልማት ፀጋዎችን አሟጦ በመጠቀም የማህበረሰቡን ኑሮ ለማሻሻል እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በመደመር መንግሥት ከማህበረሰቡ ለሚነሱ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የህዝብን የልማት ጥያቄዎች በፍጥነት በመመለስ የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል የሚከናወኑ ተግባራት በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

በተለይ የማህበረሰቡን አቅም በማስተባበር ልማትን ከማፋጠን ባለፈ ለህዝብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንደሚሰጥ ነው ያመለከቱት።

የክልሉ መንግሥት የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል እንዲሁም ሰላምን በዘላቂነት አጠናክሮ ለማስቀጠል በቁርጠኝነት ይሰራል ሲሉም አረጋግጥዋል። 

የከምባታ ዞን የመደመር መንግሥት የትኩረት አቅጣጫ በሆነው በተቀናጀ ግብርናና በሌማት ትሩፋት ትግበራ ላይ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ፀጋዬ ሞጬ (ዶ/ር) ናቸው።


 

በዚህም አርሶ አደሩ ተጠቃሚነቱን ከማረጋገጥ ባለፈ ትርፍ አምርቶ ገበያ እያረጋጋ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ በዞኑ ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ይጠናከራሉ ብለዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በላይነሽ አለሙ እንዳሉት መንግሥት በከተማና በገጠር የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ በርካታ የልማት ስራዎች እያከናወነ ይገኛል።

በቀጣይም ይህን የህዝብ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የታቀዱ የልማት ግቦች እንዲሳኩ እንደነዋሪ ለልማቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ሌላው በምክክር መድረኩ የተሳተፉት አቶ ግርማ ከለቾ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ የመደመር መንግሥት የማህበረሰቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረገ አሰራሮችን በመተግበር ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።

በመደመር መንግስት የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የታየውን ቁርጠኝነት አድንቀው፣  ለአካባቢያቸው ልማት መፋጠን የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።

በመድረኩ ላይ የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) ጨምሮ የክልል፣ የዞንና የዱራሜ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከተለያየ መዋቅር የተወጣጡ የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም