ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክትን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክትን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አደረጉ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክትን በይፋ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትሰስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በዛሬው ዕለት ለታሪካዊቷ ጎንደር እና ለአካባቢዋ ማህበረሰብ ትልቅ የምስራች የሆነውን የመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት በይፋ መርቀን ለአገልግሎት አብቅተናል ብለዋል።
ይህ ፕሮጀክት ረጅም ዓመታት የዕቅድና አተገባበር መጓተት ቢፈታተነውም፣ በመደመር እሳቤ የአፈጻጸም ችግሮቹን በመፍታት ወደ ታላቅ በረከት መለወጥ መቻሉን አመልክተዋል።
ይህ ግድብ 185 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ የመያዝ አቅም ያለውና ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በመስኖ በማልማት በአካባቢው የሚኖሩ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን በቀጥታ ተጠቃሚ በማድረግ የነዋሪዎችን የልማት ጥያቄ በዘላቂነት መመለስ የሚያስችል ታላቅ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ግድቡ ለጎንደር ከተማና በዙሪያዋ ላሉ ከተሞች አስተማማኝ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ከማቅረብ ባለፈ፣ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ መነቃቃትን ይዞ መምጣቱንም ጠቁመዋል።
በግድቡ ሰው-ሰራሽ ሀይቅ ዙሪያ የሚስፋፉት የከተማ ግብርና፣ መጠነ-ሰፊ የአሳ እርባታ፣ እንዲሁም ለቱሪዝም ልማት የሚሆኑ የመዝናኛ ሪዞርቶች እና ሎጆች ለአካባቢው ወጣቶች ሰፊ የስራ ዕድል የሚፈጥሩና የንግድ እንቅስቃሴውን የሚያሳድጉ መሆናቸውንም ነው ያብራሩት።
ይህን ስኬት ለእይታ ለማብቃት በጥብቅ ክትትልና ድጋፍ እውን ማድረግ የቻልን ቢሆንም፣ ጎንደር ገና ብዙ ሊሰራላት የሚገባ ከተማ እንደመሆኗ ህዝቡ በልማቱ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ እድገት ሁሉንም አካባቢዎች ያካተተና ሁሉንም ዜጋ እኩል የሚያቅፍ እንዲሆን በትጋት መስራታችንን እንቀጥላለን ብለዋል።