ቀጥታ፡

3ኛው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት በሳይንስ ሙዚየም ይካሄዳል

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ) ፦ሶስተኛው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ከጥቅምት 16 እስከ 20 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ በሳይንስ ሙዚየም እንደሚካሄድ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ

ሚኒስቴሩ የውሃና ኢነርጂ ሳምንቱን በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በዚህ ወቅት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ከፍተኛ አማካሪ ሚካኤል መሐሪ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት በሀገር አቀፍ ደረጃ መከበር ከጀመረ ዘንድሮ ሦስተኛ ዓመት አስቆጥሯል።

የመጀመሪያው መድረክ በአረንጓዴ አሻራ ጠቀሜታ ላይ ያተኮረ እንደነበር ጠቅሰው፣ ሁለተኛው መድረክ ደግሞ ውሃና ኢነርጂን ለዘላቂ ዕድገት ማዋል በሚል መሪ ቃል መካሄዱን አስታውሰዋል።

ሦስተኛው የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ባሉት አምስት ቀናት በሳይንስ ሙዚየም ይካሄዳል ብለዋል።

ጉባዔው በቀጣይ ለሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች ግብዓት የሚሆኑ ሐሳቦች የሚቀርቡበት መሆኑን ተናግረዋል።

ጉባዔው በኢትዮጵያ በውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችና የወደፊት ተግባራትን የሚያሳይ መድረክ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለአምስት ቀናት በሚቆየው ጉባዔ በተፋሰስ ጥበቃ፣ በውሃና ኢነርጂ ላይ ያተኮሩ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች በኢትዮጵያውያንና በውጭ ሀገር ባለሙያዎች የሚቀርቡበት መሆኑንም ተናግረዋል።

በጉባዔው ላይ የሀገር መሪዎች፣ ምሁራንና ባለሙያዎች ተሳታፊ ይሆናሉ ብለዋል።

በጉባዔው ላይ በየዕለቱ በተመደቡ ቀናት የአየር ንብረት፣ ኃይል፣ ውሃ፣ የውሃ ዲፕሎማሲ እና ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብት አጠቃቀም ዙሪያ ያሉ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ገልጸዋል።

እንዲሁም 15ኛው የባለድርሻ አካላት መድረክ እንደሚካሄድና በዚህም የቀድሞ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሮች ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት መድረክ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም