የክልሉን የመልማት አቅም ወደ ውጤት ለመቀየር ለቅንጅታዊ ተግባራት ትኩረት ተሰጥቷል- ርዕሰ መስተዳድር ፍቅሬ አማን - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን የመልማት አቅም ወደ ውጤት ለመቀየር ለቅንጅታዊ ተግባራት ትኩረት ተሰጥቷል- ርዕሰ መስተዳድር ፍቅሬ አማን
ቦንጋ ፣ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ)፦ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልን የመልማት አቅም ወደ ውጤት ለመቀየር ለቅንጅታዊ ተግባራት ትኩረት መስጠቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ፍቅሬ አማን ገለጹ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከካፋ ዞን የማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር "ማንሰራራት ለክልላችን ከፍታ" በሚል መሪ ሀሳብ እየተወያዩ ነው።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ እንደገለፁት፤ የክልሉን የመልማት አቅም ወደ ውጤት በመቀየር ዘላቂ ዕድገት ማስመዝገብ ይገባል።
በዚህም የክልሉን የመልማት አቅም ወደ ውጤት ለመቀየር ለቅንጅታዊ ተግባራት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።
የመደመር መንግሥትም የሕዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተደራጀ መልኩ ለመመለስ ወደ ሥራ መግባቱን አስረድተዋል።
የመድረኩ ዓላማም ከዞኑ ሕዝብ ጋር በመወያየት የጋራ አቅጣጫ በመያዝ፣ በርብርብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት መሆኑንም አብራርተዋል።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጉሴ ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው፣ የመደመር መንግሥት ሰው ተኮር ልማትን በማሳካት የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የግብዓት አጠቃቀምን ማሻሻል እና በገቢ ራስን ለመቻል የገቢ አቅምን ማሳደግ ሌላኛው ትኩረት የሚሰጠው ተግባር ነው ብለዋል።
በቱሪዝም ዘርፍ የማልማትና የማስተዋወቅ ሥራዎችን አጠናክሮ የማስቀጠልና ከተሞችን ለኑሮና ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የተመቹ የማድረጉ ተግባር በትኩረት እንደሚከናወንም አክለዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወንድሙ ኩርታን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከካፋ ዞን የተወጣጡ የተለያዩ የማኅበረሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።