ቀጥታ፡

የሽግግር ፍትሕ ስኬታማ እንዲሆን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ) ፦ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ የሕዝብን እምነትና ድጋፍ አግኝቶ ስኬታማ እንዲሆን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሕዝብ ግንዛቤን በማሳደግና የማኅበረሰቡን ድምፅ ለተቋማት በማድረስ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ

የፍትሕ ሚኒስቴር እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሽግግር ፍትሕ የጋራ ፎረም ምስረታ መርሃ ግብር እያካሄዱ ይገኛሉ።


 

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን ቢራቱ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከሕዝቡ ጋር ባላቸው ቅርበት፣ በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ባካበቱት ልምድና ከተጋላጭ ቡድኖች ጋር በሚያደርጉት ተሳትፎ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ አካታችና ለተጎጂዎች ተገቢውን ቦታ የሚሰጥ እንዲሆን ማገዝ ይችላሉ።

የጋራ ፎረሙ በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ ውይይትን ለማጠናከር፣ የሕዝብ ግንዛቤን ለማሳደግ፣ ለተቋማዊ ለውጦች የሚያግዙ ምክረ ሐሳቦችን ለማቅረብና በተለያዩ ድርጅቶች መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር ቋሚ መድረክ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

ፎረሙ የድርጅቶችን ጥረት ለማቀናጀት፣ የሥራ መደጋገምን ለመቀነስና የተሳታፊ ድርጅቶችን ነፃነትና ተጠያቂነት በማክበር የጋራ ሥራዎችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ እንደሚያግዝም አብራርተዋል።

ባለሥልጣኑ የሽግግር ፍትሕ ሂደቱን ለማገዝ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከሲቪል ማኅበራት ምክር ቤትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል።

የተቋማዊ ትብብርን ማጠናከር፣ የተጎጂዎችንና የተጋላጭ ቡድኖችን ውክልና ያረጋገጠ ተሳትፎ ማበረታታት፣ የዕውቀትና የአቅም ግንባታ ድጋፍ ማድረግ፣ የቴክኒክና የፋይናንስ ሀብት ማሰባሰብና የፎረሙን ዘላቂነት ማረጋገጥ በትብብር ከሚሠራባቸው ዋና ዋና መስኮች መካከል መሆናቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አሕመድ ሁሴን በበኩላቸው፤ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ያለፉ በደሎችን በመመርመር እውነትን ከማውጣትና ለተጎጂዎች ፍትሕ ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ለእርቅ፣ ለዘላቂ ሰላምና ለሀገራዊ መግባባት መሠረት የሚጥል ሂደት መሆኑን ገልጸዋል።

የሽግግር ፍትሕ የጋራ ግንዛቤና መግባባትን በመፍጠር፣ የቀደሙ በደሎችን በእውነት በመመርመርና ለተጎጂዎች ፍትሕ በማረጋገጥ ለዘላቂ ሰላም መሠረት ማኖር እንደሚቻል አመልክተዋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከሕብረተሰቡ ጋር በቅርበት የሚሠሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የተጎዱ ማኅበረሰቦችን ድምፅ በማሰማት፣ የሕዝብ ግንዛቤን በማሳደግ፣ የሴቶችን፣ የወጣቶችንና የተገለሉ ማኅበረሰቦችን ተሳትፎ በማረጋገጥ እንዲሁም በተለያዩ ወገኖች መካከል ውይይትና መተማመንን በማጠናከር ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።

የሽግግር ፍትሕ የመንግሥትና የፍትሕ ተቋማት ብቻ ኃላፊነት ሳይሆን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን፣ የመገናኛ ብዙኅን ተቋማትን፣ ምሁራንንና አጠቃላይ ማኅበረሰቡን የሚያሳትፍ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል።

የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ አሳታፊ፣ ግልጽና በሕግና በሰብዓዊ መብቶች መርሆዎች ላይ የተመሠረተ እንዲሆን የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የፍትሕ ሚኒስቴርም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም