ቀጥታ፡

የሽግግር ፍትሕ የሰላም ግንባታንና የሕግ የበላይነትን ለማጠናከር ወሳኝ ነው - ሚኒስትር ሐና አርዓያስላሴ

አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ) ፦የሽግግር ፍትሕ የሕግ የበላይነትን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስትር ሐና አርዓያስላሴ ገለጹ።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ

የፍትሕ ሚኒስቴር እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሽግግር ፍትሕ የጋራ ፎረም ምስረታ መርሃ ግብር እያካሄዱ ይገኛሉ።


 

የፍትሕ ሚኒስትር ሐና አርዓያስላሴ በዚህ ወቅት፤ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን ለማዘጋጀት ከረዥም ጊዜ ጀምሮ የጥናትና የምክክር ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በዚህም በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በርካታ መድረኮች መካሄዳቸውንና ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ሐሳቦች መሰብሰባቸውን አንስተዋል።

ፖሊሲው በመንግሥት ምክር ቤት ከጸደቀ በኋላ ለተግባራዊነቱ የሚያስፈልጉ ሕጋዊ ማዕቀፎችን የማዘጋጀት ሥራ መከናወኑን ጠቁመዋል።

የሽግግር ፍትሕ ሂደትም በግጭቶች ምክንያት የተፈጠሩ ቁርሾዎችን ለመፍታት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዳግም እንዳይፈጸሙ ለመከላከልና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የሽግግር ፍትሕ ሂደቱም የግጭቶችን መነሻ ምክንያቶች ለይቶ ለመፍታት፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ የተከማቹ ቁርሾዎችን ለማስወገድና ግጭቶች በድጋሚ እንዳይከሰቱ ለመከላከል አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከሀገራዊ ምክክር ሂደት ጋር የሽግግር ፍትሕ ሥራዎችን በማቀናጀት የሀገሪቱን የሰላም ግንባታ ጥረት ማጠናከር እንደሚገባም አመልክተዋል።

በቀጣይም የሕግ ማዕቀፎቹን በሕዝብ ተሳትፎ አጠናቆ የማጽደቅና በፖሊሲውና በሕጎቹ የተመለከቱ ተቋማትን በማቋቋም ወደ ተግባራዊ አፈጻጸም እንደሚገባ አብራርተዋል።

በዚህ ሂደት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለይም የመብት ጥሰት ሰለባዎች፣ ሴቶችና ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሂደቱ ውስጥ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው የማገዝ ሥራዎችን ጠቅሰዋል።

የሽግግር ፍትሕ ላይ ግንዛቤን ማሳደግ፣ የምርምር ሥራዎችን ማከናወንና የአፈጻጸሙን ሂደት መከታተል ከሚጠበቅባቸው ተግባራት መካከል እንደሆነም ገልጸዋል።

የሽግግር ፍትሕ ሂደት ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ መማርን እንደሚጠይቅ ጠቁመው፣ የሀገሪቱን ታሪካዊ ሁኔታና ማኅበራዊ እውነታ ያገናዘበ አተገባበር ማስፈለጉን አስረድተዋል።

የሂደቱ ስኬት በተደረጉ ስብሰባዎችና የዝግጅት ሥራዎች ባሻገር እውነትን በማፈላለግ፣ ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ ፍትሕን በማስፈንና ወደፊት የመብት ጥሰቶች እንዳይደገሙ የሚያግዙ ተቋማዊ ለውጦችን በማምጣት መመዘን እንደሚገባ አመልክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም