አመራሩ ውጤታማ ተግባር በመፈጸም የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ አለበት - ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
አመራሩ ውጤታማ ተግባር በመፈጸም የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ አለበት - ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)
ወላይታ ሶዶ፤ ጥቅምት13/2019 (ኢዜአ)፦አመራሩ በጊዜ የለንም መንፈስ ውጤታማ ተግባር በመፈጸም የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ አለበት ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
"ጊዜ የለንም፤ ከሹመት ወደ አገልግሎት፤ ከዕቅድ ወደ ተግባር ፤ ከተግባር ወደ ውጤት" በሚል መሪ ሃሳብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት አመራሮች በተለየ መልኩ አቅደው ወደ ተግባር በመግባት በውጤት የሚለካ ተግባር እንዲያከውኑ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው።
በክልሉ የህዝቡን የልማት ፍላጎት አውን ለማድረግ በየደረጃው ያለው አመራር የአስተሳሰብና የተግባር ለውጥ በማድረግ ለህዝብ ተጠቃሚነት ተግቶ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
"ህዝብን በተጨባጭ ተጠቃሚ የሚያደርገው ሪፖርትን አሳምሮ ማቅረብ ሳይሆን የአመራሩ ውጤታማ ተግባር መሆኑን ተገንዝበን ሁላችንም ልንተጋ ይገባል" ብለዋል
በተለይ ሀገራዊ የልማት ዕቅዶችን መሰረት በማድረግ የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በተለየ መልኩ በመፍታት ምላሽ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ክልሉ ያለውን እምቅ የልማት አቅም በአግባቡ ለይቶ ወደ ሀብት በመቀየር የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል የተያዙ ግቦች እንዲሳኩ በተለየ ትኩረትና ትጋት መስራት ይጠበቃል ሲሉም አሳስበዋል።
በየደረጃው አመራሩ ህዝቡን አስተባብሮ የልማት ተግባራትን በመምራት በጊዜ የለንም መንፈስ ሌት ተቀን በመትጋት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መረባረብ አለበት ብለዋል።
የክልሉ ህዝብ የሚያነሳቸው የልማት ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙ ከመንግስት ጎን በመሆን ድጋፉን እንዲያጠናክርም አመልክተዋል።
በመድረኩ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) እና የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ካሰች ኤልያስን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ አመራሮችም ተገኝተዋል።