ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት ብሎም ለብሄራዊ ጥቅሟ መከበር በላቀ ዝግጁነት ላይ እንገኛለን - የሠራዊቱ አባላት

አዳማ፣ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ)፡-ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት ብሎም ለብሄራዊ ጥቅሟ መከበር የትኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል በላቀ ዝግጁነት ላይ እንገኛለን ሲሉ የሠራዊቱ መኮንኖችና አባላት ተናገሩ።

ትልቅ አገር፣ ትልቅ ህዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ቀን በየዓመቱ ጥቅምት 15 ቀን በተለያዩ ሀገራዊና ወታደራዊ ስነ-ስርዓቶች የሚከበር መሆኑ ይታወቃል።

ዕለቱ ሲከበር ሠራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነትና የሕዝብን ሰላም ለማስጠበቅ በጀግንነት የከፈለውንና እየከፈለ ላለው ዋጋ ክብርና ምስጋና ለመስጠት ነው።

የመከላከያ ሠራዊት ቀን ሲከበር ሰራዊቱ ለሀገር ከሚከፍለው ዋጋ ባለፈ ለአሀጉራዊና ቀጣናዊ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እያበረከተ ያለው የላቀ አስተዋጽኦ አብሮ መነሳቱ አይቀርም።

ከዚህም በተጨማሪ ሰራዊቱ የውስጥ አንድነቱን፣ ወታደራዊ ዝግጁነቱን እና ዘመናዊ የውጊያ አቅሙን በማሳየት የሀገር አስተማማኝ መከታ መሆኑን የሚያሳይበት አጋጣሚም ነው። 

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከሕዝብ ጋር ያለውን ጠንካራ ትስስር  በማጠናከር፣ ሀገራዊ አንድነትን፣ ልማትንና ሰላምን ዘላቂ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማሳደግ እንደ ትልቅ መድረክ የሚያገለግል ይሆናል።

የዘንድሮው የመከላከያ ሰራዊት ቀንም የፊታችን እሁድ የድል ሰራዊት በሚል መሪ ሃሳብ በደማቅ ስነ ስርአት የሚከበር መሆኑ ይታወቃል።

የእለቱን መከበርና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም የሰራዊቱን ዝግጁነት በተመለከተ ኢዜአ ከመከላከያ ሰራዊት መኮንኖችና አባላት ጋር ቆይታ አድርጓል።

የሠራዊቱ 202ኛ ኮር ተወርዋሪ ኮከብ የዘመቻ ኃላፊ ሻለቃ ዮሴፍ ወልዴ፤ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በዘመናዊ አደረጃጀትና በላቀ ቴክኖሎጂ ታግዞ የሀገሩን ክብርና ሉአላዊነት ለማስከበር ከመቸውም ጊዜ በላይ ዝግጁነት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

የጀግንነት ውርሱን በላቀ መልኩ በማስቀጠል በተለይም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ በስልጠና እና በላቀ ዝግጁነት የትኛውንም ተልእኮ በላቀ ብቃት መፈፀም የሚችል ሰራዊት መገንባቱንም አንስተዋል።

በመሆኑም ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት ብሎም ለብሄራዊ ጥቅሟ መከበር የትኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል በላቀ ዝግጁነት ላይ እንገኛለን ብለዋል።


 

የ202ኛ ኮር መሠረታዊ ወታደር ሀይደር ነጅብአወል፤ ለውትድርና ሙያ ባለው ክብርና የሀገር ፍቅር ከዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ድግሪ እንደተመረቀ ሠራዊቱን መቀላቀሉን ይናገራል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊትን መቀላቀል ትልቅ ክብርና ኩራት መሆኑን አንስቶ ለሀገሩ ሉአላዊነት የትኛውንም መስዋእትለት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ ዝግጁነት፣ ተልእኮ የመፈፀም ብቃትና ጀግንነቱ የሀገር አስተማማኝ መከታ መሆኑን የሚያረጋግጥ መሆኑን የሠራዊቱ አባላት ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም