ቀጥታ፡

ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋሻና መከታችን ነው- የሀርቡ ከተማ ነዋሪዎች

ደሴ፣ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ)፡- ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለሉዓላዊነታችን መስዋዕትነት በመክፈል ሰላማችንን የሚያፀና ጋሻና መከታችን ነው ሲሉ በደቡብ ወሎ ዞን የሀርቡ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን ሠራዊቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ የመጣውን የጀግንነት፣ የነጻነት እና የሉዓላዊነት አስጠባቂነት ታሪክ የሚዘከርበት ታላቅ ሀገራዊ በዓል ነው። 

ይህ ቀን ሠራዊቱ ውርጭና ብርድ፣ ዝናብና ፀሐይ ሳይበግረው በዱር በገደሉ እየተዋደቀ የህዝብንና የሀገርን ሰላም እንዲሁም ደህንነት ለማረጋገጥ የሚከፍለው መስዋዕትነት በውል የሚታሰብበት ነው።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በድምቀት የሚከበረው ይህ በዓል፣ ዜጎች ከመከላከያ ሠራዊታቸው ጎን በመሰለፍ ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት የሚገልጹበት ልዩ አጋጣሚ ነው። 

በተለይም ወጣቱ ትውልድ የሠራዊቱን የጽናትና የአልሸነፍ ባይነት ታሪክ እየተማረ፣ ለሀገራዊ አንድነትና ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ትልቅ መነቃቃትን ይፈጥራል።

ዕለቱን አስመልክተው ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች፤ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለሉዓላዊነታችን መስዋዕትነት በመክፈል ሰላማችንን የሚያፀና ጋሻና መከታችን ነው ብለዋል።

የሠራዊቱ ቀን መከበሩ ትውልዱ የሀገር መከላከያን ጀግንነት፣ ታሪክ፣ ተጋድሎና ዋጋ እንዲገነዘብ ዕድልን የሚፈጥር በመሆኑ ወጣቱ ትውልድ ከምንም ነገር በላይ ለሀገሩ ዘብ እንዲቆም ያደርገዋል ሲሉም አክለዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ይገዙ ጉታይ፣ የመከላከያ ሠራዊት ቀን ሠራዊቱ ሀገርን በማጽናት ለህዝብ ጋሻ፣ መከታና ኩራት መሆኑ የሚዘከርበት ዕለት ነው ብለዋል።

ሠራዊቱ ውርጭና ብርድ፣ ዝናብና ፀሐይ ሳይበግረው በዱር በገደሉ እየተዋደቀ ጭምር በብርቱ ክንዱ የህዝብንና የሀገርን ደህንነት በመጠበቅ እያረጋገጠ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

ሠራዊቱ እየከፈለ ያለው መስዋዕትነትና ያስገኘው የሠላም ውጤት የህዝብ ልጅ፣ ለህዝብ የሚኖር አለኝታና መከታችን መሆኑን በተግባር አሳይቷል ሲሉም ገልጸዋል።


 

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ዑስማን ሠይድ በበኩላቸው፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የጀግንነት፣ የአይበገሬነትና የአልሸነፍ ባይነት ምሳሌያችን በመሆኑ ኮርተናል ብለዋል።

"መከላከያ ሠራዊት የህዝብና የሀገር ጋሻ ሆኖ የዘለቀ የኢትዮጵያ የሉዓላዊነትና የነጻነት ዋስትና ነው" ያሉት አቶ ዑስማን፣ ከሠራዊቱ ጎን ተሠልፈን ዘላቂ ሠላምና አንድነትን እናስቀጥላለን ብለዋል።

የሠራዊቱ ቀን መከበሩ ትውልዱ የሀገር መከላከያን ጀግንነት፣ ታሪክ፣ ተጋድሎና ዋጋ እንዲገነዘብ የሚያስችል በመሆኑ በጉጉት እንደሚጠብቁት ገልጸዋል።

ወጣቱም ሠራዊቱን በፍቅር በመደገፍ ከጎኑ መሠለፍ እንዳለበት ጠቁመው የነገ አገር ተረካቢ መሆኑን ማስመስከር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ሠራዊቱ የሀገር ዳር ድንበር እንዲከበር በማድረግ ሠንደቅ ዓላማችን ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ፣ በነጻነትና በኩራት እንድንኖር ያደረገን ጋሻና መከታችን ነው ብለዋል።


 

የከተማው ነዋሪ ወጣት ሚፍታህ አህመድ በበኩሉ፣ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመሠለፍ ዘላቂ ሠላምና ሀገራዊ አንድነትን ከማስጠበቅ ባለፈ ለብሔራዊ ጥቅም መከበር የበኩላችንን እንወጣለን ብሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም