የሀገር መከላከያ ሠራዊት የተገነባበት መንገድ፣ የትጥቅ አቅሙና የመፈጸም ችሎታው የሚያስደንቅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የተገነባበት መንገድ፣ የትጥቅ አቅሙና የመፈጸም ችሎታው የሚያስደንቅ ነው
ወላይታ ሶዶ፤ ጥቅምት 13/2019(ኢዜአ)፦ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የተገነባበት መንገድ፣ የትጥቅ አቅሙና የመፈፀም ችሎታው የሚያስደንቅ መሆኑን የቀድሞ ሠራዊት መኮንኖች ገለጹ።
ኢትዮጵያ ጠንካራና ዘመናዊ ሠራዊት መገንባቷ ለሉአላዊነቷ መከበርና ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢዜአ በወላይታ ሶዶ ከተማ ያነጋገራቸው የቀድሞ ሠራዊት አባላት፤ ሠራዊቱ የሀገሪቱን ዳር ድንበር ለማስከበር የማይተካ ሕይወቱን ጭምር አሳልፎ የሚሰጥ የጀግንነት ምልክትና የሀገር የፅናት ተምሳሌት መሆኑን አንስተዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የቀድሞ የሠራዊቱ አባላት መካከል ሻለቃ ጳውሎስ ገብረስላሴ፤ መከላከያ ሠራዊት ከጊዜ ወደ ጊዜ በቴክኖሎጂ እየዘመነ ከመምጣት ባለፈ በህዝባዊነቱ፣ በብቃቱና በጀግንነቱ የሚታወቅ ነው ብለዋል።
መከላከያ ሠራዊት ከራሱ ይልቅ ለሀገሩና ለህዝቡ የሚኖር አለኝታ መሆኑን ገልጸው፣ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተግባር ተልዕኮውን በሚገባ በመወጣትም ኢትዮጵያ በአፍሪካ የደህንነት ጉዳዮች ጠንካራ ተሳትፎና ጉልህ ሚና እንዲኖራት አድርጓል።
በየዘመናቱ የሀገርን ሉዓላዊነት ለመድፈር የመጣን የውጭ ወራሪ ኃይል በጀግንነት መክቶ በመመለስ ሉአላዊነቷን ጠብቆ ያቆየ የሀገር ባለውለታ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በላቀ ሙያ የተካነ፣ በዲሲፕሊን የታነጸ እና ሀገሩንና ሕዝብን በክብር የሚያገለግል ጠንካራ ሠራዊት ተገንብቷል ብለዋል።
ሠራዊቱ ከተገነባበት መንገድ በተጨማሪ በትጥቅ አቅሙ እያደገና እየዘመነ መምጣቱ በትክክልም የሀገር መከታነቱ መጠናከሩን ያሳያል ብለዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰንድቅ ዓላማችን አለኝታ ነው ያሉት ሌላኛው የቀድሞ የሠራዊት አባል ሻምበል ብዙነህ ዮሐንስ በበኩላቸው ሀገር የጸናችው በሠራዊቱ ጥንካሬ መሆኑን አንስተዋል።
ዘላቂ ሰላም በሌለበት ልማት እንደማይኖር ገልጸው፤ ሠራዊቱ የህዝብን ሰላምና ደህንነት በማስከበር የሀገር ዋልታና መከታ መሆኑን በተግባር አሳይቷል ብለዋል።
በየጊዜው የመጡ የውጭ ወራሪዎችን፤ ዛሬም የባዳዎችን ተልዕኮ ተቀብለው የሚንቀሳቀሱ ባንዳዎችን ሴራ በማክሸፍ ሀገርን ለማጽናት እየከፈለ ባለው ዋጋ ታላቅ ክብርና ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።
ለእዚህ ሠራዊት ከጎኑ በመሰለፍ ደጀንነትን ማሳየት የዜጎች ሁሉ አደራና ሃላፊነት መሆኑን የገለጹት ሻምበል ብዙነህ፣ በአሁኑ ወቅትም ሀገር የተደቀነባትን ሥጋት ቀድሞ የሚመክት ጠንካራ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መገንባቱን አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ሉአላዊነቷን የሚያስጠብቁ ጀግኖችን ቢኖራትም፣ ዛሬም ከመከላከያ ሥራዊት ጎን በመቆም ለሀገሬ ሉዓላዊነት በማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ ሲሉም አረጋግጠዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ማገልገላቸውን የተናገሩት መቶ አለቃ አካሉ ህዝቅኤል በበኩላቸው ሠራዊቱ ውድ ሕይወቱን፣ ደሙንና እጥንቱን ያለስስት ለሀገርና ለህዝብ የሚከፍል መሆኑን አንስተዋል።
መከላከያ ሠራዊት የማንም ወገን ሳይሆን ሀገርንና ህዝብን የሚወክል ብሔራዊ ተቋም መሆኑን አንስተው፣ ሀገርን ለመድፈር የሚመጡ ጠላቶችን በጀግንነት መክቶ ኢትዮጵያን ሲያጸናና ሲያስከብር የኖረ በመሆኑ ክብር ይገባዋል ብለዋል።
በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የሚደቀኑ ማናቸውንም ስጋቶች በላቀ ብቃት መመከት የሚችል ጠንካራ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በመገንባቱም ኩራት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል።