ቀጥታ፡

በጥንት ጀግኖች ተጠብቃ የቆየችውን ሀገር ክብሯንና ሉአላዊነቷን አስጠብቆ ለቀጠለው ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት የላቀ ክብር ይገባዋል

​ገንዳውኃ፣ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ)፡- በጥንት ጀግኖች ተጠብቃ የቆየችውን ሀገር ክብሯንና ሉአላዊነቷን አስጠብቆ ለቀጠለው ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት የላቀ ክብር የሚገባው መሆኑን አርበኞችና የቀድሞ የሠራዊት አባላት ተናገሩ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቀን የፊታችን እሁድ የድል ሠራዊት በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር መሆኑ ይታወቃል።

የዕለቱን መከበር በማስመልከት ኢዜአ በምእራብ ጎንደር ዞን ከሚኖሩ አባት አርበኞች እና የቀድሞ ጦር አባላት ጋር ቆይታ አድርጓል።

አባት አርበኞቹና የቀድሞ የሰራዊቱ አባላትም በጥንት ጀግኖች ተጠብቃ የቆየችውን ሀገር ክብሯንና ሉአላዊነቷን አስጠብቆ ለቀጠለው ጀግናው የመከላከያ ሰራዊት የላቀ ክብር የሚገባው መሆኑን ገልጸዋል።

በገንዳ ውኃ ከተማ የሚኖሩት አርበኛ በቀለ ጀመረ፤ የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት አስጠብቆ በመቀጠል ረገድ የቀድሞ አባቶችና እናቶች እንዲሁም የቀድሞ ሰራዊት አባላት ብዙ ዋጋ መክፈላቸውን አስታውሰዋል።

የአሁኑ ሰራዊት ደግሞ የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት በላቀ መልኩ ማስከበር የቻለ የሁላችንም ክብርና ኩራት ሆኗል ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት በዘመናዊ አደረጃጀት፣ ዘመኑ ባፈራው ትጥቅ እና በጀግንነት ሀገሩን በአስተማማኝ መልኩ እያስጠበቀ መሆኑን እያየን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በመሆኑም ለዚህ የሀገር አለኝታና መከታ ለሆነ ጀግና ሰራዊት ተገቢውን ክብርና ምስጋና መስጠት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ሌላኛው አርበኛ አዱኛ መለሠ፤ የቀድሞ አርበኞች የሀገርን ነጻነት ጠብቆ ለትውልድ በማስተላለፍ የሀገር ባለውለታዎች መሆናቸውን አስታውሰው ኢትዮጵያ አሁን ላይ የገነባችው ዘመናዊ ሰራዊትም ኩራት መሆኑን ተናግረዋል።


 

የቀድሞ ሰራዊት አባል የነበሩት ዳኘ አዲስ፤ የኢትዮጵያ ወታደር እየዘመነ እና ይበልጥ እየሰለጠነ እዚህ ደረጃ ላይ መገኘቱ ሀገርንም ህዝብንም የሚያኮራ ነው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም