ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ዘንድሮ ከ18 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሩዝ ምርት ይጠበቃል

ባህርዳር ፤ ጥቅምት 13/2019 (ኢዜአ) ፦ በአማራ ክልል በዘንድሮው የመኸር ወቅት በሩዝ ሰብል ከለማው መሬት ላይ ከ18 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የሩዝ ልማት አስተባባሪ ወይዘሮ እንዬ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መንግሥት ከውጭ የሚገባውን የሩዝ ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት ያደረገው ጥረት አበረታች ውጤት አስገኝቷል።

በዘንድሮው የመኸር ወቅት በክልሉ ለሩዝ ሰብል ልማት ተስማሚ በሆኑ ዘጠኝ ዞኖች በኩታ ገጠም የግብርና ስነዘዴ 265 ሺህ 538 ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን ገልጸዋል።


 

ከ317 ሺህ 500 በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ ከለማው የሩዝ ሰብልም ከ18 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።

ዘንድሮ የለማው መሬት ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ56 ሺህ 900 ሄክታር መሬት ብልጫ እንዳለው ጠቁመው፣ በአሰባሰብ የሚደርስ የምርት ብክነትን ለመቀነስ ዘመናዊ ማሽኖች ተሰራጭተዋል ብለዋል።

ከውጭ የሚገባውን የሩዝ ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት የተያዘውን ግብ ለማሳካት በተደረገው ጥረት በክልሉ በሩዝ ሰብል የሚለማው መሬት እየጨመረ መምጣቱን አመልክተዋል።

በደቡብ ጎንደር ዞን የፎገራ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር መለሰ መንግሥት ዘንድሮ በሩዝ ሰብል ግማሽ ሄክታር መሬታቸውን ማልማታቸውን ገልጸዋል።

የሩዝ ሰብሉን ፈጥኖ በማንሳትም በመስኖ ልማት ጤፍ፣ ሽንኩርትና ሌሎች ሰብሎችን በማልማት የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን ከወዲሁ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

በምርት ዘመኑ በሩዝ ሰብል ካለሙት አንድ ሄክታር መሬት 30 ኩንታል ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር አለባቸው ቸሬ ናቸው።

በክልሉ ባለፈው ዓመት በሩዝ ሰብል ከለማው 208 ሺህ 636 ሄክታር መሬት ከ15 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም