የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦች ተፈጻሚ እንዲሆኑ አበክሮ ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦች ተፈጻሚ እንዲሆኑ አበክሮ ይሰራል
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 12/2019 (ኢዜአ) ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦች ተፈጻሚ እንዲሆኑ አበክሮ ይሰራል ሲሉ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አህመድ ሽዴ ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ያዘጋጀው የእውቅና እና ምስጋና መርሃ ግብር አካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ፍቃዱ ተሰማ፣ የምክር ቤቱ አባላት፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሙያ ማህበራት፣ የመንግሥት ተወካዮች፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጨምሮ አሳታፊ በሆነ መልኩ ሰፋፊ ምክክሮችን በማድረግ የአጀንዳ ልየታ ስራ አከናውኗል።
በኢትዮጵያ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን በምክክርና በመግባባት እንደሚፈቱ ያሳየ ትልቅ ውጤት የተገኘበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
አራት ሺህ ኢትዮጵያዊያን መክረው ለሀገር ግንባታ መሰረት አኑረዋል ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ለሰለጠነ የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ አወንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አብራርተዋል።
ምክር ቤቱ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን በአዋጅ ከማቋቋም ጀምሮ ለስራዎቹ ስኬትማነት ሃላፊነቱን ሲወጣ መቆየቱንም አንስተዋል።
በቀጣይም በምክክሩ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ እንዲሁም ወደ ህግ የሚቀየሩ ጉዳዮችም ተቀይረው ስራ ላይ እንዲውሉ ምክር ቤቱ አበክሮ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያን ማገልገል ለኛ ክብር ነው፤ ዛሬ የተሰጠን እወቅናም በክብር የምንቀበለው ነው ብለዋል።
ምክክሩን ውጤታማ ለማድረግ ኮሚሽኑ አካታች ሂደትን መከተሉን አመልክተው፤ የምክክሩ ሂደት በዓለም አቀፍ ደረጃም ጭምር አውቅና የተቸረው መሆኑን ተናግረዋል።
በምክክሩ የተለዩ ምክረ ሀሳቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ የባለድርሻ አካላት ሚና ሊጠናከር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የኮሚሽኑ የስራ ዘመን ቢጠናቀቀም ለሀገር የምናበረክተውን አስተዋጽኦ አናቋርጥም በማለት ነው የኮሚሽኑ አመራር አባላት ያላቸውን ዝግጁነት የገለጹት።