በቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚከናወኑ የግብርና ሥራዎች የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የሀብት ምንጭ ናቸው-ግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚከናወኑ የግብርና ሥራዎች የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የሀብት ምንጭ ናቸው-ግብርና ሚኒስቴር
ወልቂጤ፤ ጥቅምት 12 /2019 (ኢዜአ)፡- በቴክኖሎጂ በመታገዝና ዕውቀትን መሰረት በማድረግ እየተተገበሩ ያሉ የግብርና ሥራዎች የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የሀብት ምንጭ መሆናቸውን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ገለፁ።
ሚኒስትር ዴኤታዋ እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዑስማን ሱሩር፤ የተቀናጀ የበጋ የግብርና ሥራዎችን በጉራጌ ዞን በእኖርና ቸሃ ወረዳ አስጀምረዋል።
በሁለቱ ወረዳዎች በኩታ ገጠም የለሙ የተለያዩ ሰብሎች በሥራ ኃላፊዎቹ ምልክታ ተደርጎባቸዋል።
በወረዳው በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ በተሰማሩ ባለሀብት ከአንድ ሺህ ሄክታር በሚልቅ ማሳ ላይ በሶስት ወራት ውስጥ የሚደርስ የበቆሎ ምርጥ ዘር ብዜት ሥራም ተጀምሯል።
በወቅቱም ሚኒስትር ዴኤታዋ እንደተናገሩት፤ በቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚከናወኑ የግብርና ሥራዎች የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ የሀብት ምንጭ ናቸው።
ባለሀብቱ የግብርናውን ዘርፍ የገቢ ምንጭ ከማድረግ ባለፈ ለዕውቀት ሽግግር፣ ለሥራ እድል ፈጠራ፣ ለምግብ ዋስትና እና ለውጪ ንግድ እድገት ከፍ ያለ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሀገሪቱ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች ስኬታማ ከመሆን ባለፈ ዘርፉ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ መሆኑን በተግባር እያሳዩ ነው ብለዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ የምርጥ ዘር እጥረት እንዳይገጥም ባለሀብቱን በማሳተፍ የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዑስማን ሱሩር በበኩላቸው፤ የውሃ አማራጮችን ሁሉ በመጠቀም በመስኖ መልማት የሚችል መሬት እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ በአንዳንድ አካባቢዎች የገጠመውን የኤልኒኖ የዝናብ እጥረት ለመቋቋም የበጋ መስኖ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በበጋ መስኖ በሶስት ወራት ውስጥ የሚደርስ የበቆሎ ምርጥ ዘርን በመዝራት የምርትና የእንስሳት መኖ እጥረትን በመፍታት የአምራቹን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አቶ ኡስማን ተናግረዋል።
በክልሉ በተቀናጀ የበጋ የግብርና ሥራ 149 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት ከ38 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መብራቴ ወልደማርያም በበኩላቸው፤ በተቀናጀ የበጋ መስኖ ልማት ከ28 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ እየለማ መሆኑን አንስተዋል።
ይህም ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና አዳዲስ የምርት ዘዴዎችን በመጠቀም የምርትና ምርታማነት እድገትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዞኑ በመኸር ወቅት ከለማው 30 ሺህ ሄክታር ማሳ ውስጥ 25 ሺህ ሄክታሩ በኩታ ገጠም የግብርና ስነ-ዘዴ መልማቱንም አስተዳዳሪው አስረድተዋል።