የመደመር መንግሥት እሳቤን የሚያጸኑና ወደ ተግባር የሚቀይሩ የጥናትና ምርምር ስራዎች ተደራሽ እየተደረጉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት እሳቤን የሚያጸኑና ወደ ተግባር የሚቀይሩ የጥናትና ምርምር ስራዎች ተደራሽ እየተደረጉ ነው
አዲስ አበባ ፤ ጥቅምት 12/2019 (ኢዜአ) ፦የመደመር መንግሥት እሳቤን የሚያጸኑና ወደ ተግባር የሚቀይሩ የጥናትና ምርምር ስራዎች ተደራሽ እየተደረጉ መሆኑን የፖሊሲ ጥናት ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ጸጋ ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ
የመደመር መንግሥት የብዝኅ ኢኮኖሚ የግብርና፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን እና አይሲቲ (ICT) ዘርፎችን በመለየት አዳዲስ የልማት አድማስ ማስፋት ችሏል።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ጸጋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ የሀገሪቷን ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት የሚያረጋግጡ ፖሊሲዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እውን በማድረግ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው።
በሀገሪቷ የመደመር እሳቤ በሁሉም መስኮች ተግባራዊ መደረጉ ለተለያዩ ዘርፎች ስኬታማነት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው ብለዋል።
የመደመር መንግሥት በጥናትና ምርምር የታገዘ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ግንባታ ምኅዳርን ለማስፋት ያሳየው ቁርጠኝነት ለኢንስቲትዩቱ ትልቅ አቅም እንደፈጠረለትም አንስተዋል።
የብዝኅ ኢኮኖሚ ዘርፍ የትኩረት መስኮች ጸጋን ለይቶ በማልማት በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ የምርታማነት ዕድገትን ማስመዝገብ እንዲቻል ኢንስቲትዩቱ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ለዘርፎቹ ተደራሽ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
ለዚህም ከዘርፎቹ ጋር አቻ የሆኑ የምርምር ማዕከላትን በማቋቋምና ባለሙያዎችን በመመደብ በትኩረት እየሠራ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በዓመት 40 የምርምር ውጤቶችን ተደራሽ ማድረግ ችሏል ነው ያሉት።
ከዚህ ጎን ለጎን የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳይ ሌላኛው የትኩረት መስክ መሆኑን ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዘርፉ አስቻይና ውጤታማ የጥናትና ምርምር ሥራ ትኩረት ተሰጥቶታል።
በመሆኑም በስምንት ዓመት ውስጥ በግብርና መስክ የተካሄዱ ጥናቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የተደረገ ሲሆን፣ ይህም ለፖሊሲ እና ስትራቴጂ ማሻሻያዎች ግብዓት በመሆን ዘርፉ ፈጣንና እምርታዊ ለውጥ እንዲያመጣ አስችሏል ብለዋል።
በተጨማሪም በኢንዱስትሪና በቤት ልማት ዙሪያ የተጠኑ መፍትሔ አመላካች ትልልቅ ጥናቶችም እንዲሁ ተደራሽ የተደረጉ ሲሆን፣ ይህም ዘርፉ ፈጣን ዕድገት እንዲያስመዘግብ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
የጥናትና ምርምር ሥራ ለዘርፎች አዳዲስ አማራጮችን በማመላከት ውጤታማነትን ለማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተለይም የመደመር መንግሥት እሳቤን የሚያሠርጹና ለተግባራዊነቱ አመላካች የሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎች በስፋት በመሥራት ተደራሽ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።