ቀጥታ፡

በክልሉ የኩነት ምዝገባ አሠራርን ወደ ዲጂታል በማሸጋገር ከፍተኛ ሀብትና ጊዜን ከብክነት መታደግ ተችሏል

ባህር ዳር፣ጥቅምት 12/ 2019 (ኢዜአ) ፡-በአማራ ክልል የኩነት ምዝገባ አሠራርን ወደ ዲጂታል በማሸጋገር ከፍተኛ ሀብትና ጊዜን ከብክነት መታደግ ማስቻሉን የክልሉ የሲቪልና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት አስታወቀ።

የአገልግሎቱ ዋና ኃላፊ መዓዛ በዛብህ የሩብ ዓመቱን አፈጻጸም አስመልክተው ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በክልሉ የኩነት ምዝገባ አሠራርን ወደ ዲጂታል በማሸጋገር ከፍተኛ ሀብትና ጊዜን ከብክነት መታደግ ተችሏል።

በዚህም አገልግሎቱ በሩብ ዓመቱ 421 ሺህ 300 በላይ ኩነቶችን ለመመዝገብ ግብ ይዞ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

ዕቅዱን ለማሳካትም በቴክኖሎጂ የተደገፈ የልደት፣ የሞት፣ የጋብቻ፣ የፍቺ እና የጉዲፈቻ ኩነቶችን በመመዝገብ የሩብ ዓመት ዕቅዱን 67 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።

በቀበሌ እና በወረዳ ደረጃ ለሚሰጡ አገልግሎቶች ውጤታማነት የነበረውን የሰው ኃይል ክፍተት 95 በመቶ የማሟላትና የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን በስፋት መከናወኑ ተጠቃሽ መሆኑን አመልክተዋል።

በአንድ ማዕከል አሠራር ህጻናት በጤና ተቋም ወዲያው እንደተወለዱ መመዝገብ መቻሉ የእናቶችን እንግልት ከማስቀረቱም በላይ አሠራሩን ወደ ሌሎች ፋሲሊቲዎች የማስፋት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በዲጂታላይዜሽን ዘርፍ ቀደም ሲል በኦንላይን ምዝገባ ከገቡት 774 የምዝገባ ጣቢያዎች በተጨማሪ በሩብ ዓመቱም 435 የምዝገባ ጣቢያዎችን ወደ ዲጂታላይዜሽን ለማስገባት ለባለሙያዎች የክህሎት ሥልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።

በቀጣይም ሥራውን አጠናክሮ በማስቀጠል ሁሉንም የምዝገባ ጣቢያዎች በቀጥታ ወደ ዲጂታል ምዝገባ ሥርዓት እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።

በዚህም ቀደም ሲል በዲጂታል አሠራር ምዝገባ በተጀመረባቸው ጣቢያዎች ለወረቀትና ለቅጽ መግዣ እንዲሁም ለትራንስፖርት ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ሀብት ከወጪ ማዳን መቻሉንም አብራርተዋል።

የአገልግሎቱን አፈጻጸም መሬት ላይ ለማረጋገጥ የክልል ቴክኒክ ቡድን እስከ ቀበሌና ጤና ጣቢያ በመውረድ የተቀናጀ ድጋፍና ክትትል ማድረጉንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም