የሀገር ልዕልና በጠንካራ ተቋማት - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር ልዕልና በጠንካራ ተቋማት
በማሬ ቃጦ
የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት፤ የሉዓላዊነት ዋልታ፣ የሕዝብ ደኅንነት ጋሻ፣ የብሔራዊ ጥቅም ዘብ
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ
የሀገር ታላቅነት ከሰነቀችው ርዕይ ባሻገር ርዕዩን በተግባር በሚያሳኩ አስተማማኝ ተቋማት ይለካል። ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ ያላት ኢትዮጵያ የምትመኘውን የልማት፣ የሰላምና የብልፅግና ግብ ለማሳካት አስተማማኝ ተቋማትን በጽኑ መሠረት ላይ በመገንባት ላይ ትገኛለች። በተለይም ሰላምን የሚያስጠብቁ፣ ደኅንነትን የሚያረጋግጡ፣ የሕግ የበላይነትን የሚያሰፍኑና የዜጎችን መብት የሚያስከብሩ ተቋማት የሀገራዊ ልማት ዋነኛ መሠረቶች ናቸው።
ሰላም ልማትን የሚያፋጥን መሠረታዊ ሁኔታ ነው። ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎችን በማሳለጥ የተረጋጋ አካባቢያዊና ሀገራዊ ምኅዳር ለመፍጠር የዜጎች ልዕልና እንዲሁም የፀጥታና ደኅንነት ተቋማት አስተማማኝነት ያስፈልጋል። ይህንን እውን ለማድረግ የመከላከያ ሠራዊት፣ የፖሊስ፣ የመረጃና ደኅንነት ተቋማት፣ የፍትሕ አካላትና የሰላም ግንባታ ተቋማት ሕጋዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
ኢትዮጵያም በሰነቀችው ታላቅ ርዕይ መሠረት የሕዝቧን ታላቅነት የሚመጥኑ የፀጥታና ደኅንነት ተቋማትን እየገነባች ትገኛለች። የኢትዮጵያና የሕዝቦቿ ታላቅነትም ሰላምን በማስጠበቅ፣ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥና ተቋማቷን በዘመናዊ ዕውቀትና በሙያዊ ብቃት በማጠናከር በሚወስዷቸው ተግባራዊ እርምጃዎች ይለካል።
የመደመር መንግሥት የተቋማት የሪፎርም እርምጃ የዜጎችን ደኅንነትና አመኔታ በማስጠበቅ፣ በወንጀል መከላከል፣ በግጭት አፈታትና በፍትሕ አገልግሎት ውጤታማ አቅም ለመገንባት ያለመ ነው። በዚህም የሰው ሃይል ልማትን፣ ሙያዊ ሥልጠናን፣ የመረጃ ትንተናን፣ የአመራር ብቃትን፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምንና የሎጂስቲክስ ዝግጁነት አቅም ገንብተዋል። የተቋማቱ የሥራ ባህልም ከትዕዛዝ መቀበልና ማስተላለፍ ወደ ችግር ፈቺነት፣ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ አሰጣጥና ተከታታይ የአፈጻጸም ማሻሻያ እንዲሸጋገር ትኩረት ተሰጥቷል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ሉዓላዊነትና የድንበር ደኅንነት የመጠበቅ ሕገ-መንግሥታዊ ኃላፊነት የተሸከመ ብሔራዊ ተቋም ነው። ታሪካዊ ጀግንነቱና ለሀገር ልዕልና የከፈለው መስዋዕትነትም በሕዝብ ልብ ውስጥ የታተመ ነው። ሠራዊቱ ከሀገር ውስጥ ባሻገር በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር መድረኮች የገነነ ስምና ዝናን ያተረፈ የሰላም ዘብ ነው። ይህንን ታሪካዊ ውርስ በማስቀጠል የመደመር መንግሥት ሠራዊቱን ሙያዊ ገለልተኝነቱን የጠበቀ፣ የዘመኑን ቴክኖሎጂ የታጠቀና በከፍተኛ ዕውቀትና ሙያዊ ዲሲፕሊን የሚመራ ተቋም በማድረግ ላይ ይገኛል።
የመከላከያ ሠራዊቱ ጥራት ያለው ሥልጠና፣ የአመራር ብቃት፣ የመረጃ አጠቃቀም፣ የድጋፍ ስልት፣ የማምረትና የጥገና አቅም የሀገር ዘብ እንዲሆን ያስችሉታል። የቴክኖሎጂ ዕድገትም በዘመናዊ የደኅንነት ሥርዓት ውስጥ ወሳኝ ሚና አለው። የድሮን ቴክኖሎጂ፣ የመረጃ ሥርዓቶች፣ የዲጂታል ቁጥጥርና የምርምር አቅም ለመከላከያ ተግባራት ወሳኝ መሠረቶች ናቸው።
በኢትዮጵያም የድሮን ቴክኖሎጂ ማምረትን ጨምሮ የሀገር ውስጥ የመከላከያ ቴክኖሎጂ አቅምን ለማሳደግ የሚደረጉ ጥረቶች በምርምር፣ በምህንድስና፣ በሙያተኛ ልማትና በኢንዱስትሪ ግንባታ ላይ ያተኮሩ የረጅም ጊዜ ዕቅዶች አካል ናቸው። ይህም ኢትዮጵያ በውጭ ቴክኖሎጂ ላይ ያላትን ጥገኝነት በመቀነስ የራሷን የፈጠራ አቅም ለማሳደግ ዕድል ይፈጥራል።
ስካይዊን ኤሮናውቲክስ ኢንዱስትሪ መከፈትም በሀገር ውስጥ የድሮን ቴክኖሎጂን ለማሳደግ ከተወሰዱ እርምጃዎች አንዱ ነው። የኢትዮጵያ የድሮን ቴክኖሎጂ ልማት ከመከላከያ ሠራዊት ባሻገርም ፋይዳ አለው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የድሮን ቴክኖሎጂን በተመለከተ በአንድ ወቅት በሰጡት ማብራሪያ፤ የሀገር ልጆች በአጭር ጊዜ ውስጥ ቴክኖሎጂውን ከመረዳት ባለፈ ማምረት መቻላቸው አኩሪ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ሐሳብ የሀገር ውስጥ የሰው ኃይልና የፈጠራ ችሎታ በተገቢው ድጋፍ ሲታገዝ ቴክኖሎጂን ከመጠቀም ወደ ማምረት መሸጋገር እንደሚቻል ያሳያል።
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት፣ ፖሊስ፣ የመረጃና ደኅንነት ተቋማት፣ የፍትሕ አካላትና የሰላም ተቋማት የሪፎርም እርምጃዎች የማድረግ አቅማቸውን ለማጎልበት ያለሙ ናቸው። የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ለሕዝብ ደኅንነት የሚሠሩ በመሆናቸው፣ ሕግን አክብረው ማስከበር፣ የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅና የሕግ የበላይነትን ማስፈን ዋነኛ ኃላፊነታቸው ነው።
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የግጭት መንስኤዎችን በጥልቀት መረዳት፣ የሕግ የበላይነትን ማጠናከር፣ የማኅበረሰብ እርቅን ማበረታታትና ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱ ሥርዓቶችን ማሳደግ ወሳኝ ነው። የደኅንነት አቅም ከእነዚህ ሥራዎች ጋር ሲጣመር ሰላምን በረጅም ጊዜ ለማስጠበቅ ዘላቂ መሠረት ይፈጥራል።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ ያላት ኢትዮጵያ መሻት በታሪካዊ ኩራትና በብሔራዊ ምኞት ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን በዘመናዊ ተቋማት፣ በሙያዊ ብቃት፣ በሕግ የበላይነትና በሕዝብ ደኅንነት የሚረጋገጥ ተግባራዊ ርዕይ ነው።
የኢትዮጵያ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ግንባታ ዋና ግብ በሀብትና በመዋቅር የበለጸጉ ተቋማትን ከመፍጠር ባሻገር የሀገርን ሉዓላዊነት የሚጠብቁ፣ የዜጎችን ደኅንነት የሚያረጋግጡ፣ የሕግ የበላይነትን የሚያስከብሩና ለተለዋዋጭ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የደኅንነት ሥጋቶች የሚቋቋሙ ተቋማትን መገንባት ነው። ይህንን ለማሳካት ሪፎርምን ከዕቅድ ወደ ተግባር፣ ሥልጠናን ወደ ተግባራዊ ብቃት፣ የቴክኖሎጂ ግዥን ወደ ሀገር ውስጥ ፈጠራና ምርት፣ እንዲሁም ተቋማዊ ቅንጅትን ወደ የተሻለ ውጤት የሚያሸጋግር ተቋማዊ አቅም መገንባት ያስፈልጋል።
ታላቅ ርዕይ የሚረጋገጠው በታላቅ ሐሳብ፣ በጠንካራ ተቋማት ግንባታ፣ በሙያዊ ብቃት፣ በተጨባጭ ውጤትና በሕዝብ እምነት ነው። የኢትዮጵያ የሰላምና ደኅንነት ተቋማትም በዕውቀትና በሙያዊ ሥነ-ምግባር እየተመሩ ሉዓላዊ አንድነቷንና ክብሯን ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል።
የመከላከያ ሠራዊት የአየር ኃይልና የምድር ኃይል የማድረግ አቅም፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢንሳ) የቁልፍ መሠረተ ልማት ጥበቃ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የመረጃ ሥርዓት፣ እንዲሁም የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት የሪፎርም እርምጃዎች የጠንካራ ሀገር ግንባታ አካላት ናቸው።