ቀጥታ፡

በአፋር ክልል የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የማዘመን ስራው ተጠናክሯል

ሠመራ፣ጥቅምት 12/2019 (ኢዜአ)፡-በአፋር ክልል  የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማሻሻል የህብረተሰቡን እርካታ ለማረጋገጥ ትኩረት መደረጉን የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ገለጸ።

ሁለተኛው ዙር የአፋር ክልል የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር የሪፎርም ትግበራ ማስጀመሪያ መድረክ በሠመራ ከተማ ተካሄዷል።


 

በመድረኩ የተገኙት የአፋር ክልል ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ አህመድ እንዳሉት፤ የመንግሥትን የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ የአገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋና ጥራትን ያማከለ መሆን አለበት።

ለዚህም በክልሉ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማሻሻል የህብረተሰቡን እርካታ ለማረጋገጥ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።

መንግሥት የአገልግሎት አሰጣጡ በቴክኖሎጂ የታገዘና ቀልጣፋ እንዲሁም ጥራት ያለው እንዲሆን የተገበረው የሪፎርም ሥራ በአገር አቀፍ ደረጃ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም በመጀመሪያው ዙር የተከናወኑ ተግባራት ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ የማሸጋገር ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ የማገዝ ተግባራት የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ የሚያስችል መሆኑን የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል።

ተገልጋዩ ህብረተሰብ በእያንዳንዱ አገልግሎት እርካታውን የሚገልጽበትን አሰራር በፍጥነት ለመዘርጋት እንደ ሀገር የተጀመረውን የሪፎርም አካል ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑንም አብራርተዋል።

ሁለተኛውን ዙር የመንግሥት አገልግሎትና አስተዳደር የሪፎርም ስራዎችን በመተግባር የህብረተሰቡን ቀጣይ ፍላጎት በማሟላት የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ እንደሚያስችልም አመልክተዋል።


 

በቢሮው የለውጥ ዳይሬክተር አቶ አህመድ ኢድሪስ በበኩላቸው፤ የሪፎርም ትግበራው የአገልግሎት አሰጣጡን በማላቅ ቀልጣፋና በዲጂታል የታገዘ አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል እንደሆነ ጠቁመዋል።

በዚህም የመንግሥት ተቋማት ውጤታማ ለመሆን በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ፣ በሙያ፣ በክህሎትና በዕውቀት የበለጸገ የሰው ኃይልን መጠቀም ግድ ይላል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም