የዘንድሮው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከርና ለጋራ ብልፅግና ቃል የሚታደስበት ነው - ምክትል አፈ ጉባኤ ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
የዘንድሮው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከርና ለጋራ ብልፅግና ቃል የሚታደስበት ነው - ምክትል አፈ ጉባኤ ደስታ ሌዳሞ
ጅማ፤ ጥቅምት 12/2019(ኢዜአ)፡-የዘንድሮው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከርና ለጋራ ብልፅግና ዳግም ቃል የሚታደስበት ነው ሲሉ የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
21ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን አስመልክቶ የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ደስታ ሌዳሞ እና የሁሉም የክልል አፈ ጉባኤዎችና ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት የምክክር መድረክ በጅማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
ምክትል አፈ ጉባኤ ደስታ ሌዳሞ በወቅቱ፤ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በሀገራዊ ትርክት እና በጋራ ታሪክ ላይ በመመሥረት ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከርና ለኢትዮጵያ ብልፅግና የጋራ ቁርጠኝነትን ለማደስ ወሳኝ መድረክ ነው ብለዋል።
በዓሉ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ የሚከበር እና የሀገሪቱ ኩራት የሆኑ የሁሉም ብሔሮች አኩሪ ባህሎች በጋራ በአደባባይ የሚደምቁበት መሆኑንም ተናግረዋል።
እለቱ ብሔር ብሔረሰቦች የቆዩ ግንኙነቶቻቸውን የሚያጠናክሩበት፣ ለሀገራዊ ዓላማዎች በጋራ የሚተጉበትና ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያን ለመገንባት የጋራ ቁርጠኝነት የሚያሳድጉበት እንደሆነም ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈም፣ የዘንድሮው በዓል የሰዎች መሰባሰብ ብቻ ሳይሆን በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር፣ በውይይት የጋራ ችግሮችን ለመፍታትና ለሀገራዊ አንድነት የሚያግዙ የጋራ እሴቶች የሚንጸባረቁበት መድረክ መሆኑን አመልክተዋል።
በዚህ መሠረት በዓሉ በጅማ ከተማ በድምቀት እንደሚከበርም ምክትል አፈ ጉባዔው ጠቁመዋል።