ቀጥታ፡

በአስተዳደሩ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርታማነትና ጥራት በላቀ ደረጃ በማሳደግ የተገኙ ስኬቶች ይጠናከራሉ

ድሬደዋ፣ ጥቅምት 12/2019(ኢዜአ)፡-በድሬዳዋ አስተዳደር የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርታማነትና ጥራት በላቀ ደረጃ በማሳደግ የተገኙ ስኬቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአስተዳደሩ ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ።

በድሬዳዋ አስተዳደር የካይዘን ፍልስፍና ትግበራ ውጤቶችን በተቀናጀ መንገድ ለማስቀጠል ያለመ የዕውቅና መድረክ ዛሬ ተካሄዷል።


 

በመድረኩም የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ፣ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር እንደገለጹት፤ በአስተዳደሩ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርታማነትና ጥራት በላቀ ደረጃ በማሳደግ የተገኙ ስኬቶች ይጠናከራሉ።

የአምራች ኢንዱስትሪዎች የምርታማነትና ጥራት ማደግም የገበያ ዋጋን ለማረጋጋትና በሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶች የውጭ ምንዛሬን ለማዳን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት የካይዘን ፍልስፍና ትግበራ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ማሳደግ አስችሏል ብለዋል።

ለአብነትም የፍልስፍናው ትግበራ በ2016 በጀት ዓመት ከነበረበት 52 በመቶ በ2018 ዓ/ም ወደ 67 ነጥብ 5 በመቶ ከፍ ያደረገ ሲሆን፣ የምርት አቅርቦቱንም በ90 በመቶ ማሳደግ አስችሏል ብለዋል።

በተጨማሪም ለማሽኖች ጥገና ሲወጣ የነበረን  68 ሚሊዮን ብር ከማዳኑም ባሻገር 13 ሺህ 400 ካሬ ሜትር ቦታን ጥቅም ላይ ማዋል መቻሉን አስረድተዋል።


 

የዛሬው መድረክ ዋና ዓላማም በፍልስፍናው ትግበራ የላቀ አፈጻጸም ላሳዩ ኢንዱስትሪዎችና ተቋማት ዕውቅና በመስጠት፣ ልምዱን ወደ ሌሎች ተቋማት ማስፋፋት እንደሆነም አመልክተዋል።

ዕውቅና ከተሰጣቸው ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የድል ጮራ ሪፈራል ሆስፒታል የለውጥ ስራ አስተባባሪ ወይዘሮ ፀደይ አዲሱ፤ ከካይዘን ትግበራ በኋላ የሆስፒታሉ አገልግሎት ፈጣንና ቀልጣፋ በመሆኑ የተገልጋዮች እርካታ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።


 

በተጨማሪም ጽዱ፣ ውብና ምቹ የስራ አካባቢ እውን በመሆኑም ለሰራተኞች የስራ መነቃቃትን ፈጥሯል ብለዋል።

በተመሳሳይም የድሬ ስቲል የብረታብረት አምራች ኢንዱስትሪ ተወካይ ኢንጂነር ታምራት ገብረህይወት በበኩላቸው፤ በካይዘን ፍልስፍና ታግዘው ተኪ የብረት ምርቶችን በጥራትና በመጠን በከፍተኛ ደረጃ ለገበያ ማቅረብ መቻላቸውን ገልጸዋል።


 

በዛሬው የዕውቅና መድረክ ላይ የተቋማትና የኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም