ቀጥታ፡

የትግራይ ወጣት አዲስ ታሪክ ይጽፋል!

የሕገ ወጡ ሕወሃት ዘመን አብቅቷል። የትግራይ ወጣት ትውልድ በአዲስ አስተሳሰብ፣ በጠንካራ ዕይታ አዲስ ታሪክ ይጽፋል።

ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ርዕይ

ከፖለቲካ ዕድገት፣ ከሕዝብ ፍላጎት እና ከለውጥ መላመድ የማይችል የሕገ ወጡ ሕወሓት ቡድን የቆየ የጫካ አስተሳሰብ የትግራይን ሕዝብ ጎድቶታል። የሚከተለው በኃይልና በቁጥጥር ላይ የተመሠረተ አሠራር ሕዝቡን ለከፋ ጦርነትና ውድመት ዳርጎታል።

ለአምሳ ዓመታት ወጣቶችና ዕድሜያቸው ከፍርድ በታች የሆኑ ሕፃናትን በኃይል እያፈሰ ለሞት፣ ጉዳትና ስደት ዳርጓቸዋል። የሀገርና ሕዝብ ሀብት ዘርፏል፤ ከእናቶች መቀነት እና ከተፈናቃይ ዜጎች የእለት ጉርሻ ቀምቷል። ማዕድን እና የክልሉን በጀት በመዝረፍ ጥቂት ባለሀብቶች ብቻ የሚጠቅሙ ነገር ግን ሰፊው ሕዝብ በሚጎዱ ሕገ ወጥ ተግባራት በንቃት ተሳትፏል።

ለዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ታሪካዊ ዕድል የከፈተውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አፍርሶ፣ ክልሉን ለአደጋ አጋልጦ ሌላ ግጭት ከፍቷል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢቢሲ በነበራቸው ቆይታ የሕወሓትን ባህሪ ሲገልጹ፤ ሰይጣን ለማስመሰል እንደሚጥረው ሁሉ ሕገ ወጡ ሕወሓት በአፉ ሰብዓዊ ለመምሰል ይለፋል፤ ስለ ሰብዓዊ ክብርም ይሰብካል፣ ይጮኻል፤ በተግባር ግን ለሰብዓዊ ክብር እና ሕይወት ቅንጣት ታክል ግድ የሌለው ሀገር አፍራሽ ስብስብ ብለውታል።

ሕገ ወጡ ሕወሓት "መሪው፣ አድራጊውና አዋቂው እኔ ነኝ" እያለ የሚመራውን ሕዝብ እያሳደደ፣ እያንገላታ፣ ያለ ፍላጎቱ ለጦርነት በመማገድ ለስቃይና መከራ የሚዳርግ ቡድን ነው። እርሱ ለዘመናት የተከተለው አመለካከት፣ ፖሊሲ እና እምነት ከትግራይ ሕዝብ ክብር ጋር የማይስማማ ፀረ-ሕዝብ መሆኑን ማሳያዎች ናቸው።

ቡድኑ ሥልጣኑን እና ጥቅሙን በጦርነት ማስቀጠል የሚፈልገው "ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል" በሚለው እሳቤው በመመራት ነው። ትግራይን እንደ ራሱ ኩባንያ፣ ሕዝቡን እንደ ሎሌው አድርጎ ለመቆጣጠር በሚመቸው መልኩ ሕዝቡን እየከፋፈለ ሲሠራ መቆየቱን ዛሬ ትግራዋይ የተገነዘበው ጉዳይ ነው።

ካለፉት መንግሥታት በማነፃፀር ትግራይ የአንድ ድርጅት ንብረት እና ርስት አለመሆኗን፣ በተለይ ትግራይ ተተኪ ትውልድ እንዳላት፣ ከእርሱ በኋላም ትግራይ እንዳትኖር ብዙ ሕገ ወጥ ሥራ መሥራቱን፤ ይህም መሬት ላይ ያለ እውነታ እና የቡድኑ እውነተኛ ተግባር እንደሆነ ሁሉም ይስማሙበታል።

ሕዝቡ፣ በተለይ የትግራይ እናቶች "ልጆቻችንን አትውሰዱብን፤ ጦርነት ይበቃል፤ ሰላም ይሻላል" ብለው ሲቃወሙ፤ ቡድኑ ግን የዳቦ ስም እየሰጠ ለራሱ ቡድናዊ ዓላማ ሲል ሰፊውን ሕዝብ ለከፋ ጉዳት፣ ስደት፣ እስር እና ሞት ሲዳርግ ቆይቷል።

የፌዴራል መንግሥት "ግጭት አያዋጣም፣ ሰላም ይሻላል፤ ልዩነቶችን በሰላማዊ ውይይት እንፍታ" ብሎ በተደጋጋሚ ቢማፀንም፣ ሕገ ወጡ ሕወሓት ግን ለተሰጠው ምክር ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ከተለያዩ ኃይሎች ጋር በመተባበር ግጭት በመፍጠር የተላላኪነት ሚና ለመወጣት ሲፍጨረጨር ተስተውሏል።

ሕዝቡ በተደራራቢ ችግር ውስጥ ሆኖ፣ መሠረተ ልማቶች ዘግቶ ዳግም ግጭት መቀስቀሱ ለሕዝብ ደንታ የሌለው መሆኑን ራሱ በድጋሜ አስመስክሯል።

ሕገ ወጡ ሕወሓት በአፉ ሕዝባዊ ሊመስል፣ በተግባሩ ግን ፀረ-ሕዝብ ስለመሆኑ በተግባር አረጋግጧል። ትናንት በየመድረኩ "ሕገ-መንግሥት" እያለ ሲመጻደቅ እንዳልነበረ፣ ዛሬ ሕገ-መንግሥቱን ከማይቀበሉ ኃይሎች ጋር ተባብሮ መሥራቱ በእርግጥም የሚያስገርም ነው።

ለትግራይ ሰላም የፖለቲካ ምርጫ ብቻ አይደለም፤ የሕዝቧን ሕይወት የማዳን፣ የተበታተነ ማኅበራዊ ሕይወት የመጠገን መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ይህም መጪው ትውልድ በሰላም፣ በደኅንነት እና በተስፋ ላይ የተመሠረተ ሕይወት እንዲገነባ የማይተካ ቅድመ ሁኔታ ነው።

ባለፉት ዓመታት በጦርነት የተጎዳችው ትግራይ፣ ዛሬ ከሁሉ በላይ ከጥፋት የምትከላከልበት ብቻ ሳይሆን፣ ወደ አዲስ የግንባታ እና የልማት ምዕራፍ የምትሸጋገረበትን አዲስ መንገድ መፈለግ ይኖርባታል።

አሁን የትግራይ ሕዝብ ጥያቄ ሰላምን ማጽናት፣ ልማትን ማፋጠን፣ የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን መልሶ መገንባት፣ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው መመለስ፣ ሰብዓዊ ድጋፍ ማቅረብና መደበኛ ሕይወታቸውን እንዲጀምሩ ማስቻል መሆኑን እየገለጸ ነው። ይህም የዘላቂ ሰላም የመጀመሪያው መለኪያ ሲሆን መንግሥትም በትኩረት እንደሚሠራበት አረጋግጧል።

ለዚህም ነው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በጦርነቱ ሳቢያ በትግራይ የደረሰውን ልማታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት አቅልሎ እንደማይታይ፣ አሁንም ወጣቱ ለድርጅት እና ለድርጅት መሪዎች ብሎ ከሚሞትና ክላሽ ተሸክሞ ከሚንከራተት ክላሹን አውርዶ ወደ ልማት መመለስ እንዳለበት፣ በትግራይ መልሶ ግንባታ ላይ እንዲሳተፍ ምክራቸውን የለገሱት።

ቃል ወደ ተግባር፣ ተስፋ ወደ ዕድል፣ ሰላምም ወደ እውነተኛ ልማት መቀየር እንዳለበት የብዙዎች እምነት ቢሆንም፣ የትግራይ ሕዝብ ወደ ሰላም እንዲመለስ በውጭና በውስጥ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች፣ በተለይ ወጣቱ ትውልድ አካሉን እና አእምሮውን ለልማት ማዋል አለበት የሚለውን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልዕክት ተግባራዊ ማድረግ ግድ ይላል።

ከእንግዲህ ወዲያ የትግራይ ሕዝብ ጭቆና የሚቀበልበት ጫንቃ የለውም፤ የኢትዮጵያ መታወቂያ ይዘው ዜግነታቸውን የሚክዱና የኢትዮጵያ ሀብት እየዘረፉ አስመራን የሚናፍቁ ጦርነት ጠማቂዎች ቦታ የላቸውም። ይህ የወጣቱ ትውልድ አዲስ አመለካከት ነው።

የክልሉ ሕዝብ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር በመተባበር ሰላሙን ለማጽናትና የልማትና የአንድነት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እየተካሄዱ ባሉ የሕዝብ ውይይቶች መግባባት ላይ ተደርሷል።

ይህ ለትግራይ ሕዝብ ብሎም ለመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም እና የተስፋ ዜና ሲሆን፣ የትግራይ ወጣት ከሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን በመላቀቅ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር የሚያደርግ መሆኑ ታምኖበታል።

የሕገ ወጡ ሕወሓት ታሪክ አክትሟል፤ የትግራይ ወጣቱ ትውልድም በአዲስ ምዕራፍና በአዲስ ተስፋ ትግራይን መልሶ ለመገንባት ሚናውን ይወጣል።

ሕወሓት እየከሰመ፣ ወደፊት ታሪክ እየሆነ ነው። ከዚህ በፊት ከነበሩት የኢትዮጵያ መሪዎች የሚለይ አይደለም። የትግራይ ሕዝብ ግን አለ፣ ይኖራል፣ ይቀጥላል፤ መሪዎች እና ድርጅቶች ይነሳሉ፣ ይወድቃሉ። መንግሥታትም ይለዋወጣሉ፤ ሕዝብ እና ሀገር ግን ይቀጥላሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም