በክልሉ በመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በኢነርጂና በማዕድን ዘርፎች የህዝብን ተጠቃሚነት ያሳደጉ ሥራዎች ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በኢነርጂና በማዕድን ዘርፎች የህዝብን ተጠቃሚነት ያሳደጉ ሥራዎች ተከናውነዋል
ቦንጋ፣ጥቅምት12/2019 (ኢዜአ):-በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባለፉት ሦስት ወራት በንጹህ መጠጥ ውሃ፣ በአማራጭ ኢነርጂና በማዕድን ዘርፍ የህዝብን ተጠቃሚነት ያሳደጉ ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።
የክልሉ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮና የተጠሪ ተቋማት የ2019 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ተካሂዷል።
የቢሮው ሀላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው በዚህ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ ባለፉት ሦስት ወራት በንጹህ መጠጥ ውሃ፣ በአማራጭ ኢነርጂና በማዕድን ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት የህዝቡን ተጠቃሚነት አሳድገዋል።
በክልሉ ህብረተሰቡ በስፋት ከሚያነሳቸው ጥያቄዎች መካከል የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እንዱ እንደሆነ አንስተው፣ ችግሩን ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት የክልሉን የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን 46 በመቶ በማድረስ ከ108 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ መያዙንም አመልክተዋል፡፡
በዚህም በሩብ ዓመቱ በተሰሩ ሥራዎች ብቻ ቁጥራቸው 37 ሺህ የሚጠጋ የህብረተሰብ ክፍሎችን የንፁህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ነው የገለጹት።
በተጨማሪም 139 ሺህ ዜጎችን የአማራጭ ኢነርጂ ተጠቃሚ ለማድረግ በተያዘው ግብ መሰረት ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ 43 ሺህ 390 የሚሆኑትን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ቢሮ ሀላፊው ተናግረዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፣ አርሶ አደሩን ከውሃ ጠባቂነት አላቆ የመስኖ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
ለእዚህ በክልሉ በመስኖ የሚለማን መሬት ሽፋን ወደ 4ሺህ 773 ሄክታር ለማድረስ መታቀዱን ጠቁመው፣ ትላልቅ የመስኖ አውታሮችን ለመገንባት የጥናትና ዲዛይን ሥራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ ብለዋል።
የማዕድን ሀብትን በአግባቡ በመምራትና በማስተዳደር በበጀት ዓመቱ ከ400 ኪ.ግ በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ለማድረግ መታቀዱንም አመልክተዋል።
ዕቅዱ እንዲሳካም ለአዳዲስ ማህበራት ፍቃድ የመስጠትና ነባሮቹን የማጠናከር እንዲሁም የግብይት ስርዓቱን የማዘመን ሥራ ተሰርቷል ሲሉም ገልጸዋል።
በየደረጃው ያሉ መዋቅሮች በውሃ ፕሮጀክቶች ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ ማድረግና በማዕድን ሀብት ላይ የሚስተዋሉ ሕገወጥነትን በቅንጅት መከላከል ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሆኑም አስታውቀዋል።
የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጉሴ ወልደጊዮርጊስ፣ የዞኑ ሕዝብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ በስፋት ሲነሳ የነበረውን የንፁህ የመጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ እስካሁን በተከናወኑ ሥራዎች የዞኑ የንፁህ የመጠጥ ውሃ ሽፋን እያደገ ቢመጣም አሁንም በከተማና በገጠር ችግሩ በስፋት ስለሚስተዋል የተቀናጀ ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።
በመድረኩ ላይ የተጠሪ ተቋማት የሥራ ሀላፊዎችና የዞን ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።