ህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን ለትግራይ ህዝብ ምንም ያልፈየደ ቀኑም ሌቱም የጨለመበት የተበተነ ሃይል ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
ህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን ለትግራይ ህዝብ ምንም ያልፈየደ ቀኑም ሌቱም የጨለመበት የተበተነ ሃይል ሆኗል
ህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን ለትግራይ ህዝብ ምንም ያልፈየደ ቀኑም ሌቱም የጨለመበት የተበተነ ሃይል ሆኗል - አረጋዊ በርሄ (ዶር)
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2019 (ኢዜአ)፦ህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን ለትግራይ ህዝብ ምንም ያልፈየደ ቀኑም ሌቱም የጨለመበት የተበተነ ሃይል ሆኗል ሲሉ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀ መንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ገለጹ።
አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ህገ ወጡ የህወሃት ቡድን ህዝቡንና ወጣቶችን ከጎዳና እያፈሰ ለጦርነት በማሰለፍ ስልጣኑን ለማስቀጠል ያደረገው ጥረት የጨለመበትና የመከነ አስተሳሰብ ውጤት ነው።
የኢትዮጵያ በተለይም የትግራይ ህዝብ ይህ ህገ ወጥ ቡድን ከስልጣን መውረዱን ተከትሎ የሄደበትን መንገድና የፈጸመውን እኩይ ተግባር እንዳወቀበትም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ደጋግሞ የሰላም ጥሪዎችን ማድረጉንና እስከ ፕሪቶሪያ ድረስ መሄዱንም አስታውሰዋል።
ነገር ግን ህገወጥ ቡድኑ በሰላም ጊዜ ተጠያቂ እንደሚሆን ስለሚያውቅ ግርግርና ሁከትን በመፍጠር ሁኔታዎችን ለማራዘም ደፋ ቀና ሲል መቆየቱን ገልፀው፤ ይህ ዓይነቱ አደገኛ አካሄድ የማይሆንና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አመልክተዋል።
በዚህም ህገወጡ የህወሃት ቡድን ለትግራይ ህዝብ ምንም ያልፈየደ ቀኑም ሌቱም የጨለመበት ሃይል ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል።
የትግራይ ህዝብ በህገ ወጡ የህወሃት ቡድን ምክንያት በጦርነትና በሰቀቀን በመሰላቸቱ ምክንያት ልጆቹንና ሀብቱን አሳልፎ ላለመስጠትና ግጭትም እንደማይፈልግ በግልጽ ሰልፍ ወጥቶ ተቃውሞውን አሰምቷል ብለዋል።
የኢትዮጵያዊነት መሰረት ከስሜት ባለፈ በታሪክ፣ በባህል እና በጥንታዊነት የፀና መሆኑን የጠቆሙት ሊቀ መንበሩ፣ ሀገራችን የረጅም ዘመን ታሪካዊ ጸጋ ያላት ሀገር መሆኗን አስረድተዋል።
የትግራይ ህዝብም ለአንድነቱና ለኢትዮጵያዊነቱ ቀናኢ እና ስር የሰደደ ኢትዮጵያዊነት በህዝቡ ውስጥ እንደሚገኝ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ጥምረት “ፅምዶ” በሚል ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተቋቋመው ስብስብ ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶችና ከውስጥ አላማ አስፈጻሚዎች ጋር የተመሰረተ ሴራ መሆኑን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ እንድትፈርስ የሚፈልጉ እንደ ግብፅ ያሉ የቆዩ ጠላቶች እና የግብፅ ተባባሪ የሆነው የሻዕቢያ ሃይል ከህወሃት አመራሮች ጋር በጥምረት በመሆን የጥፋት ስብስብ አቋቁመው እንደነበር ተናግረዋል።
የህወሃት አመራር የነዚህ ሃይሎች ወኪል በመሆን ስብስቡ እንዲፈጠር ማስተባበሩን፣ መቐለ ላይ መስርተው አዋጅ በማወጅ ለመንቀሳቀስ አቅደው እንደነበረም አብራርተዋል።
ነገር ግን ይህ አደገኛ እቅድ በፍጥነት ተነቅቶበት፣ ሴራው ተስፋፍቶ ሳይሄድ ብትንትኑ እንዲወጣ መደረጉን አመልክተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የአመለካከት ልዩነቶች በውይይትና በሰላማዊ መንገድ እንደሚፈቱ ሁሉ፣ በሀገራችንም ሁሉም ዜጋ ልዩነቶችን በማጥበብ በህብረት ሊቆም እንደሚገባ መክረዋል።