ቀጥታ፡

በግብርናው ዘርፍ የሚከናወኑ ምርምሮች፣ ቴክኖሎጂዎችና ዝርያ ማሻሻያ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያመጡ ነው 

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2019 (ኢዜአ)፦ምርትና ምርታማነትን በዘላቂነት ለማሳደግ እና ሀገራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚከናወኑ የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የዝርያ ማሻሻያ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት ማምጣታቸውን የተለያዩ ክልሎች ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።

የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አስማረ ደጀን (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመበት ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሉ የሰብል፣ የአትክልትና የፍራፍሬ፣ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራትን በማከናወን ረገድ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል።

በዚህም እስካሁን በ32 ሰብሎች ላይ 190 ዝርያዎችንና ከአንድ ሺህ በላይ ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቁን አስታውቀዋል።

በእንስሳት ዘርፍ የበግ፣ የፍየልና የዶሮ ዝርያዎችን በማሻሻል፣ የእንቁላል ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ዘዴዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

በሌሎች ክልሎች የተገኙ የግብርና ምርምር ውጤቶችን ተቀብለው እንደሚያስፋፉም ተናግረዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ተረፈ በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ሦስት ዓመታት የአርሶ አደሩን ህይወት የሚቀይሩ፣ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በእጥፍ የሚጨምሩ ቴክኖሎጂዎችን የማፍለቅ፣ የማላመድና የማስፋፋት ተግባራትን ማከናወኑን አብራርተዋል።

ኢንስቲትዩቱ ከሰባት በላይ የሚሆኑ የስንዴ ምርጥ ዘር ዝርያዎችንና የሥራ ሥር ዘሮችን አባዝቶ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የክልሉን ምርትና ምርታማነት መጨመርና የግብርና ማነቆ የሆኑ ተግዳሮቶችን በምርምር መፍታት ለሀገር እድገትና ብልፅግና ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አንስተዋል።ይህም የአርሶ አደሩን ህይወት የመቀየር ዓላማ ያነገበ ተግባር መሆኑን አመልክተዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዮት መብራቴ (ዶ/ር)፤ኢንስቲትዩቱ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን፣ ዝርያዎችንና የአዘራር ሥርዓቶችን በማስረጽ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

አብዛኛው የክልሉ ህብረተሰብ ለምግብነት ከሚጠቀምባቸው ሥራ ሥሮች መካከል እንሰት አንዱ መሆኑን አንስተው፣ ይህን ዝርያ በማሻሻል ረገድ ደጋ፣ ወይና ደጋና ቆላ የአየር ንብረትን መቋቋም የሚችሉ ሰባት የእንሰት ዝርያዎችን መለየታቸውን አስታውቀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ከ700 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የአካባቢ ዝርያዎችን በመሰብሰብና በመለየት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም