ኢትዮጵያ ዘላቂና ጤናማ የምግብ ሥርዓት በመገንባት ተጨባጭ ውጤት አስመዝግባለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ዘላቂና ጤናማ የምግብ ሥርዓት በመገንባት ተጨባጭ ውጤት አስመዝግባለች
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ተመጣጣኝና ጤናማ ምግብ የሚያቀርብ፣ የሥራ ዕድል የሚፈጥርና የተፈጥሮ ሀብትን የሚጠብቅ ዘላቂ የግብርና ሥርዓት ለመገንባት በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሤ (ዶ/ር) ገለጹ።
የ2026 ዓለም አቀፍ የምግብ ቀን "ዛሬን እንፍጠር፤ ነገን እንመግብ" በሚል መሪ ሀሳብ በግብርና ሚኒስቴር፣ በተባበሩት መንግሥታት የግብርና እና የምግብ ድርጅት (FAO) እና በዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) በአዲስ አበባ ተከብሯል።
በበዓሉ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት፣ የልማት አጋሮች፣ ተመራማሪዎች፣ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች፣ እንዲሁም ወጣቶችና የግብርና ፈጠራ ባለቤቶች ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሤ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ዘርፉ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የቴክኖሎጂና የኢኖቬሽን ሽግግርን ለማፋጠን በትኩረት እየሠራች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
በፖሊሲ፣ በፕሮግራሞችና በተቋማዊ አደረጃጀቶች ላይ ማሻሻያ በማድረግም መስኖን ማስፋፋትና የግብርና ሜካናይዜሽንን ማፋጠን ላይ ትኩረት ማድረጓንም አስረድተዋል።
እንዲሁም የገበያ ሥርዓትን ማሻሻልና ዘላቂ የገጠር ኢኮኖሚ የመገንባት ሥራ ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እያደረገች ትገኛለች ብለዋል።
የአርሶ አደሩና የአርብቶ አደሩ አገር በቀል እውቀቶች ተቀናጅተው ለአየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ አሠራሮች መተግበራቸውን አመልክተዋል።
በቀጣይም የምግብ ሥርዓት ሽግግርን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የመንግሥት፣ የክልሎች፣ የተመራማሪዎች እንዲሁም የልማት አጋሮች ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) የኢትዮጵያ ረዳት ተወካይ ወርቅቾ ጃተኖ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ኢኮኖሚን ለማሳደግና ድህነትን ለመቀነስ እያደረገ ያለውን ተጨባጭ ጥረት አድንቀዋል።
ድርጅታቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አጋርነት እንደሚያጠናክርና እስከ 2030 የሚቆየውን የሀገር ውስጥ ፕሮግራም ማዕቀፍ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዝላታን ሚሊሲክ፤ ኢትዮጵያ የወጣት ኃይሏን፣ የተፈጥሮ ሀብቷን እና የሀገር በቀል እውቀቷን በመጠቀም የምግብ ሥርዓቷን ለመቀየር ያከናወነችውን ውጤታማ ተግባር አድንቀዋል።
ለዚህም መንግሥት በዘርፉ ያወጣቸው ብሔራዊ ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች ትልቅ መሠረት መጣላቸውን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ መስኖን በማስፋፋት፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር እና መስኩን ምቹ በማድረግ ረገድ የጀመረችውን የመሪነት ሚና ለማስቀጠል የተቀናጀ ድጋፍ እና ትብብር አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።