ቀጥታ፡

የስንዴ ምርጥ ዘር አቅርቦት ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው

አሰላ፤ ጥቅምት 12/2019 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምስራቅ ዞን ጥዮ ወረዳ ለአርሶ አደሮች በስፋት የቀረበው የስንዴ ምርጥ ዘር በማሳ ላይ ተጨባጭ የምርትና ምርታማነት እድገት ማስመዝገቡን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

ትልቅ አገር፣ ትልቅ ህዝብ፣ ታላቅ ርዕይ


 

በወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት የሰብል ልማትና እንክብካቤ የስራ ሂደት ሃላፊ አቶ ዘላለም ሹሚ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በጥዮ ወረዳ ከ37ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብሎች ተሸፍኗል።

በሰብል ከተሸፈነው ውስጥ 19ሺህ 123 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በስንዴ መልማቱን የገለጹት አቶ ዘላለም 15ሺህ ሄክታር የሚሆነው ደግሞ በቢራ ገብስ የለማ ነው ብለዋል።

በተለይም ከቁሉምሳ ግብርና ምርምር ማእከል  ጋር በመተባበር የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ የሚችሉ የስንዴ ምርጥ ዘር በስፋት ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።


 

በዋናነት በኩታ ገጠም ከለሙት የስንዴ ዝርያዎች መካከል መልካና አባይ የተባሉ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ዝርያዎች ሲሆን፤  በወረዳው በአርሶ አደሩ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ መሆኑንም ተናግረዋል።

ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግና በሀገር ደረጃ የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የተቀመጠው ግብ እንዲሳካ የአፈር ማዳበሪያን ጨምሮ የተለያዩ አዳዲስ አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎች በስፋት አገልግሎት ላይ መዋላቸውን ተናግረዋል።

የቤተሰብ አቅምን በማቀናጀት ፀረ-አረምና ፀረ-ተባይ መድኃኒቶችን በመጠቀም የሰብል እንክብካቤው በባለሙያዎች ደጋፊነት በዘላቂነት በመከናወኑም የሰብሉ ቁመናና የምርት ይዘቱ በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም ብጫ ዋግና የስንዴ ራስ አድርቅ በሽታዎችን ጨምሮ ምርትና ምርታማነትን የሚቀንሱ በሽታዎችንና አረሞችን ከአርሶ አደሩ ማሳ ለማስወገድ የተደረገው ጥረት ሰብሉ በተሻለ ደረጃ ላይ እንዲገኝ ማስቻሉን አቶ ዘላለም ገልጸዋል።


 

አርሶ አደር ጎሳ ነሞ በበኩላቸው፤  በኩታገጠም ተደራጅተን በ17 ሄክታር መሬት ላይ አባይ የስንዴ ምርጥ ዘር ወስደን ዘርተናል፤ ሰብሉም በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም እስከ 50 ኩንታል ምርት ከሄክታር እንጠብቃለን ያሉት አርሶ አደር ጎሳ አባይ የሚባል የስንዴ ምርጥ ዘር በአነስተኛ እርጥበት በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጥኖ የሚደርስ ከመሆኑንም ባለፈ ድርቅን የሚቋቋም መሆኑንም ተናግረዋል። 

በቁሉምሳ ግብርና ምርምር ማእከል የዘር  ተመራማሪ የሆኑት  አቶ ሃይሉ መንግስቱ እንደገለጹት፤ ማእከሉ ቴክኖሎጂን በማፍለቅ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እያደረገ ይገኛል።


 

በተለይም በምርምር ያወጣውን መነሻ ዘር ከኢትዮጰያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ፣ ከተለያዩ ዩኒየኖች እና ከዘር አባዥ ድርጅቶች ጋር በመሆን በስፋት አባዝቶ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።

መልካና አባይ የሚባሉ የስንዴ ምርጥ ዘር ማእከሉ  ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረጉን ጠቅሰው በተለይም ምርጥ ዘሩ ድርቅና የኢልኒኖ ተፅዕኖን በመቋቋም ፈጥኖ የሚደርስና ከፍተኛ ምርት የሚሰጥ ነው ብለዋል።

በሄክታር በአማካይ ከ45 እስከ 50 ኩንታል ምርት የሚሰጥ የስንዴ ዝርያ መሆኑን የገለጹት አቶ ሃይሉ አርሶ አደሩ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱንም ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም