በዲላ ከተማ ያለውን እምቅ የቱሪዝም አቅም ለመጠቀም ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በዲላ ከተማ ያለውን እምቅ የቱሪዝም አቅም ለመጠቀም ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል
ዲላ፤ ጥቅምት 12/2019 (ኢዜአ)፦በዲላ ከተማና አካባቢው ያለውን እምቅ የቱሪዝም አቅም በአግባቡ ለመጠቀም ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ልዩ ትኩረት መሰጠቱን የከተማው ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።
ጥራት ያለው የመስተንግዶ፣ የገበያና የትራንስፖርት አገልግሎት መኖር ቱሪስቶች በአካባቢው ረዘም ያለ ጊዜ እንዲያሳልፉ የራሱን ሚና ይጫወታል።
ለቱሪስቶች ደረጃቸውን የጠበቁ አገልግሎቶች መስጠትም አካባቢውን ተመራጭና ተወዳዳሪ የቱሪስት ማዕከል ከማድረግ ባለፈ በገጽታ ግንባታ በኩልም ጠቀሜታው የጎላ ነው።
የዲላ ከተማም በዩኔስኮ ከተመዘገበው የጌዴኦ ባህላዊ መልከዓ ምድር በቅርብ ርቅት ላይ ትገኛለች፤ የቡና ቱሪዝም፣ የባህልና የተፈጥሮ መስህቦች መገኛም ናት።
የከተማዋ ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ዘሪሁን ተስፋዬ እንደሚሉት ዲላና አካባቢዋ ለቱሪዝም፣ ለምርምርና ለንግድ ተመራጭ ብትሆንም የመዳረሻ ልማትና የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ውስንነት የዘርፉ ተግዳሮት ሆነው ቆይተዋል።
በመሆኑም በዲላ ከተማና አካባቢው ያለውን የቱሪዝም አቅም አውጥቶ ለመጠቀም በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በከተማው የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትን በመገንባት የቱሪዝም ገቢን ለማሳደግ ከግሉ ዘርፍ ጋር ውጤታማ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይ በአገልግሎት ዘርፍ ለሚሰማሩ የግል ባለሃብቶች የመሬት አቅርቦትን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ዘርፉን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል አምስት ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችና አንድ ሎጅ ግንባታቸው እየተጠናቀቀ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
ይህም በከተማው የጎብኚዎችን ቁጥር ከማሳደግና ከተማዋን የቱሪዝም ኮንፍራንስ ማዕከል ከማድረግ ባለፈ ከ1 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩን አንስተዋል።
በከተማዋ አልሚ ባለሃብት አቶ ዳንኤል ሙላት በበኩላቸው፤ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል እያስገነቡ የሚገኘው ኢንተርናሽናል ሆቴላቸው በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ቀሪ ስራዎችን አጠናቆ በተያዘው ዓመት ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ የልማት ሥራው ከተማዋን የቱሪዝም ኮንፍራንስ ማዕከል ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል።
ሀገራዊ የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ የቱሪዝም ዘርፉን በእጅጉ ማነቃቃቱን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ልማት ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ብዙነህ ንጉሴ ናቸው።
ማህበሩ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ሰጭ ተቋም እያስገነባ መሆኑን ጠቅሰው ይህም የማህበሩን ገቢ ከማጠናከር ባለፈ የአካባቢውን የቱሪዝም ሀብት ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።
ተቋሙ ለከተማዋ አዲስ ገጽታ እንደሚሰጥ ገልጸው፣ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍን ይበልጥ ለማነቃቃት ከተማ አስተዳደሩ ከግሉ ዘርፍ ጋር የሚያደርገው ቅንጅታዊ ሥራ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።