ሰራዊቱ ሉዓላዊቷ የተጠበቀ ሀገርን ለትውልድ ለማስተላለፍ እያደረገ ያለውን ተጋድሎ እንደግፋለን- የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሰራዊቱ ሉዓላዊቷ የተጠበቀ ሀገርን ለትውልድ ለማስተላለፍ እያደረገ ያለውን ተጋድሎ እንደግፋለን- የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች
ደብረ ብርሃን፤ ጥቅምት 12/2019 (ኢዜአ)፦ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሉዓላዊትና አንድነቷ የተጠበቀ ሀገርን ለትውልድ ለማስተላለፍ እያደረገ ያለውን ተጋድሎ እንደሚደግፉ የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የመከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በደብረ ብርሃን ከተማ ዛሬ ተካሄዷል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይም ነዋሪዎቹ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሉዓላዊትና አንድነቷ የተጠበቀ ሀገርን ለትውልድ ለማስተላለፍ እያደረገ ላለው ጥረት ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።
የሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ዮርዳኖስ ማሙዬ እንዳሉት፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ራሱን ሰውቶ ሀገርን የሚያጸና የህዝብ ልጅ በመሆኑ ለመደገፍ መውጣታቸውን ተናግረዋል።
ሰልፍ ከመውጣት ባሻገር መከላከያ ሠራዊቱን በገንዘብ፣ በጉልበትና በሌሎች ተግባራት ሁሉ ግንባር ቀደም በመሆን እንደሚደግፉም ያላቸውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
ሌላኛው የሰልፉ ተሳታፊ አቶ እሸቱ በቀለ በበኩላቸው፤ የሀገር መከታ የሆነውን መከላከያ ሠራዊትን የመደገፍ እድል በማግኘታቸው መደሰታቸውን አስረድተዋል።
ሠራዊቱ ለህይወቱ ሳይሳሳ የሀገርን ዳር ድንበር የሚያስከብር እንዲሁም ሰላምን የሚያፀና በመሆኑ ያላቸውን ክብርና ድጋፍ ገልጸዋል።
ከአባቶቻችን የወረስነውን ሀገር የማጽናት ጀግንነት ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ መሰል የድጋፍ ሰልፎች ጠቃሚ ናቸው ያሉት ደግሞ የ70 ዓመቱ የዕድሜ ባለጸጋ አቶ ለማ በላቸው ናቸው።
ትውልዱ፣ ሠራዊቱ ለሀገር ሉዓላዊነት መከበር እየከፈለ ያለውን መስዋዕትነት ሊገነዘብና ከጎኑ በመቆም የሀገርን ክብር ማስቀጠል ይጠበቅበታል ብለዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት እንደገለጹት፤ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ለጥፋት የተሰለፉ ሃይሎችን የሚያወግዝና ሴራቸውን ለማክሸፍም ያለመ ነው።
ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ለመከላከያ ሠራዊት ያለውን አጋርነት መግለጹ የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም እና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።
የመከላከያ ሰራዊታችን ዛሬም እንደ ትናንቱ ሀገርን በማጽናት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ የሚያካሂደው ትግል ውጤታማ እንዲሆን ህዝቡ የደጀንነት ሚናውን እንደሚወጣ መግለጹ ትልቅ አቅም ነው ብለዋል።
ህዝቡ በአደባባይ ወጥቶ መከላከያ ሰራዊቱን በመደገፍና ጽንፈኞችን በማውገዝ ባስተላለፈው መልእክትም የአገራችንን ሰላምና ልማት አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል መሆኑንም አረጋግጧል ብለዋል።
በደብረ ብርሃን ከተማ በተካሄደው ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይም የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።