ቀጥታ፡

የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ህብረብሔራዊ አንድነትንና አብሮነትን ለማጠናከር ጉልህ ሚና አለው

ጅማ ፤ ጥቅምት 12/2019 (ኢዜአ)፦  የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የህዝቦችን ብዝሃነትና የጋራ እሴቶች በማጎልበት ህብረብሔራዊ አንድነትንና የሀገረ መንግሥት ግንባታን ለማጠናከር ወሳኝ ሚና እንዳለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

ትልቅ አገር፣ ትልቅ ህዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

የፌዴራል እና የክልል ምክር ቤቶች አፈጉባኤዎች የዘንድሮውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በሚስተናገድበት የጅማ ከተማ በመገኘት የበዓሉን ዝግጅቶች ገምግመዋል።


 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ ደስታ ሌዳሞ በወቅቱ እንደገለጹት፣ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የህዝቦችን ብዝሃነት፣ መከባበርና የጋራ እሴቶች በማጎልበት ህብረብሔራዊ አንድነትን ያጠናክራል።

የበዓሉ መከበር እኩልነትና ዘላቂ ሰላም የሰፈነባትን ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ውስጥም ወሳኝ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

በዓሉ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦችን እሴቶች ከማጠናከሩም በላይ ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች በመሻገር የሀገር ግንባታን እንዲያጠናክሩ ያግዛል ብለዋል።

በዓሉ ሲከበርም ብዝኃነትን እንደ ውበትና ጥንካሬ በመጠቀም የሀገሪቱን ገጽታ ማሳደግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

አዲሱ ትውልድም አንድነት የጋራ ጥንካሬ መሆኑን በመረዳት የነገዋን ኢትዮጵያ ለመገንባት በትጋት መሥራት እንደሚጠበቅበት አስረድተዋል።

በምልከታው የተገኙት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አስካለች አልቦሮ በበኩላቸው፣ በዓሉ ብዝኃነትን በማጠናከር አብሮነትን ለማሳደግ፣ እንዲሁም በሕዝቦች መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከር የሚያስችል አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።


 


በዓሉ በጅማ ከተማ በድምቀት መከበሩ ከተማዋ ያላትን የቱሪዝም አቅም ለማስተዋወቅ ጠቀሜታ እንዳለውም አመልክተዋል።

በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን አስተዳዳሪ ረሻድ ከማል(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን የኢትዮጵያውያን የትስስር በዓል ነው ብለዋል።


 

በተለይም በኦሮሚያ ክልል አዲስ የዞን አደረጃጀት በተከናወነበት ወቅት መከበሩ ለአካባቢው ትልቅ ዕድል መሆኑን ጠቅሰዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞንም ሆነ የጅማ ከተማ እንግዶቿን በደማቁ ተቀብላ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን ጠቅሰው፤ በዓሉ በቱሪዝም ረገድ አካባቢው ያለውን እምቅ አቅም የበለጠ ለማጉላት ዕድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም