ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ በመንግሥት እና በህዝብ መካከል አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል መሰረት ጥሏል

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 12/2019 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምክክሩ በመንግሥት እና በህዝብ መካከል አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል መሰረት መጣሉን የሀገራዊ ምክክር  ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ።

ኮሚሽኑ የሥራ ጊዜውን ማጠናቀቁን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።


 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ኮሚሽኑ የተቋቋመበትን ዋና ዋና ዓላማዎች በማሳካት የተጣለበትን የሥራ ኃላፊነት በስኬት አጠናቋል።

ኮሚሽኑ የህዝቡን ድምፅና ፍላጎት መሰረት ያደረገ ሰፊ የምክክር ሂደት ሲያካሂድ ቆይቷል ብለዋል።

ሂደቱም ተዓማኒነት ያለው፣ አሳታፊና አካታች መርሆዎችን ባከበረ መልኩ መካሄዱንና ተቋሙ ከተጣለበት አላማ አንጻር ስራውን በብቃት መወጣቱ ጠቁመዋል።

4 ሺህ ተሳታፊዎች የተገኙበት የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተካሂዶ የተሰበሰቡ 394 ምክረ ሀሳቦች ይፋ መደረጋቸውንም ገልጸዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ተዓማኒ፣ አሳታፊና አካታች መርህን ተከትሎ መካሄዱን የጠቆሙት ዋና ኮሚሽነሩ፣ በልዩነቶች ላይ መወያየት መጀመሩ ትልቅ እርምጃና ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።

በሀገራዊ ምክክሩ ለሀገረ መንግሥት ግንባታና ለዲሞክራሲ ሥርዓት መዳበር መሰረት የሚሆኑ ጠቃሚ ምክረ ሀሳቦች መቅረባቸውን አብራርተዋል።

ሂደቱ በመንግሥት እና በህዝብ መካከል አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመዘርጋት የሚያስችል መሰረት የጣለ እንደሆነም ተናግረዋል። 

ለምክክሩ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉ ባለድርሻ አካላት ሁሉ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፣ በጥቂት ወራት ውስጥም ምክረ ሀሳቦችን በዲጂታል የመሰነድና የማስረከብ ሥራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም